Sunday, December 15, 2013

በአዲስ አበባ ከ600 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ቀጭን ትዕዛዝ ተላለፈ

የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ደሃ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ ቦታቸውን እየወሰዱ ነው

በአዲስ አበባ ከ600 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን በ3 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ኢሳት ቴሌቭዥን ዘገበ። እንደ ቲቪው ዘገባ ትእዛዙን የሰጠው የቦሌ ክፍለከተማ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ እስከ ማክሰኞ ቤታቸውን ለቀው ካልወጡ ፣ አፍራሽ ግብረሀይል በጉልበት እንደሚያፈርስባቸው አስታውቋል።
“በሶስት ቀናት ውስጥ የት እንሄዳለን?’ ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪዎች ፣በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚታየው የቤት ኪራይ መጨመር አስግቶናል ብለዋል። ሜዳ ላይ እንዃ እንዳንወድቅ ሜዳውም እየታረሰ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል ሲል ዘግቧል።
በተያያዘ ዜናም ኢሳት በዜና ዘገባው በኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ባለስልጣናት በስልጣናቸው ደሀ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ ቦታዎቻቸውን እየወሰዱባቸው ነው ሲል ዘገበ። ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው አርሶአደሮች በጉልበት መሬታቸውን እየተቀሙ ለበለጠ ድህነት እየተጋለጡ መሆኑን አስታውቋል። ከተቀሙት አርሶ አደሮች መካከል በሰበታ ነዋሪ ከሆኑት አንዱ ሲናገሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት የአቶ ደምሴ ቡላ ባለቤት መሬታቸውን በጉልበት እንደነጠቁዋቸውና ክስ ሲመሰርቱም እንዳሳሰሩዋቸው ተናግረዋል ያለው ኢሳት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ቤት ሰርተው ይኖሩ ነበሩ ሰዎች ቤቶቻቸው ከፈረሱባቸው በሁዋላ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸው ይታወቃል ሲል የዜና ዘገባውን አጠቃሏል።
Ze-Habesha

No comments:

Post a Comment