Tuesday, April 29, 2014

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ | Zehabesha Amharic


አዲስ ጉዳይ) ፖሊስ ለምርመራ 10 ቀናት ጠይቋል ባለፈው ሳምንት ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2006 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት 3 ጋዜጠኞች እና 6 ብሎገሮች ዕሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2006 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በማዕከላዊ እስር ቤት የቆዩት ተጠርጣሪዎች ሰኞ ለፍርድ እንደሚቀርቡ የተጠበቀ ቢሆንም ባልተለመደ ሁኔታ ዕሁድ እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን የክሱም ሃሳብ በአጭሩ “ሀገሪቱን በሶሻል ሚዲያ ለማተራመስ ራሱን የመብት ተሟጋች ነኝ ብሎ ከሚጠራ የውጭ ኃይል ጋር በሃሳብም በገንዘብም ተረዳድተውና ተስማምተው የብጥብጥ ቅስቀሳ ለማነሳሳት አቅደው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል” የሚል ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው ቢሆንም በ3 የተለያዩ መዝገቦች ተከፋፍለው ነው ፍርድ ቤት ቀረቡት፡፡ የአዲስጉዳይ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆነው ዘላለም ክብረት እና የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጠኛና በአሁኑ ወቅት በአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ላይ የሚሰራው ተስፋለም ወልደየስ በመዝገብ ቁጥር 118722 የተጠቃለሉ ሲሆን፤ አጥናፉ ብርሃነ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና ኤዶም ካሣ በመዝገብ ቁጥር 118721 እንዲሁም በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና አቤል ዋበላ በመዝገብ ቁጥር 118720 የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ናቸው።
በመዝገብ ቁጥር 118721 እና መዝገብ ቁጥር 118722 የተካተቱት ተጠርጣሪዎች ለሚያዝያ 29 ቀን 2006 ተቀጥረዋል። ጉዳያቸው በመዝገብ ቁጥር 118720 የተካተተው ተጠርጣሪዎች ደግሞ ለሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓመተምህረት ተቀጥረዋል።
zehabesha/amharic/archives/29599

Monday, April 14, 2014

አንድ ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ነው? ወይስ ሲፈቀድለት? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11818/

April 14, 2014
በአለፈው ሳምንት (ፋክት ቁጥር 36) ወይዘሮ መስከረም የተለያዩ መጻሕፍትን በመጥቀስ በሴቶች ላይ ያለውን መጥፎ ጫና በደንብ ያስመሰከረች ይመስለኛል፤ ግን እኮ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የቆየ፣ ክፉና ጎጂ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፤ ቁም-ነገሩ ያለው ከዚያ የባህል ጭነት በራስ ጥረት ወጥቶ፣ ነቀፌታንም ሆነ እርማትን ለመቀበል ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንደመስከረም በአደባባይ ሀሳብን በመግለጽ በአገርና በወገን ጉዳይ መሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ የተቻለን ሁሉ ማድረጉ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ይህንን መልስ የምጽፈው፤ ወይዘሮ መስከረም በአጋጠሟትና በምታያቸው እንቅፋቶች ላይ ማተኮርዋ እንደርስዋ መንፈሳዊ ወኔው የሌላቸውን ያስፈራራቸዋል እንጂ አያበረታታቸውም፤ የማንንም አፍአዊ ጫና ተቋቁመው በራሳቸው የውስጥ ኃይል እንዲመሩ እናድርግ።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
አንድ መጽሐፍን በመጥቀስ ወይዘሮ መስከረም የሚከተለውን ጽፋለች፡–
ፈጣሪ የሠራውን ውጫዊ ገጽታን ማሽሞንሞን በቂ እንደሆነ ሲነገራት የኖረች ሴት፣ በምን ተነሳሺነት አእምሮዋን የሚመግብ እውቀት ልትሻ ትችላለች? … በልጅነት እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት በጉብዝና ወራት አላዋቂ በመሆን ቢወቀስ ትርጉም አይኖረውም፤ …››
ወይዘሮ መስከረም ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው (ልብ በሉ ሴት አላልሁም፤) መሆንዋን እንዴት እስከዛሬ ሳታውቅ ቀረች? ባለመጽሐፉም ይሁን መስከረም የሔዋንን ታሪክ ሳያነሡ መቅረታቸው መሠረታዊ ስሕተት ነው፤ በተጠቀሱት ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አንድም እውነትን የሚመስል ነገር የለም፤ መስከረም‹‹የሔዋን ዘር›› ከማለት በፊት የሔዋንን ሥራ ቆም ብላ ብታስታውስ የጠቀሰችውን መጽሐፍ እኔ እንደምነቅፈው ትነቅፈው ነበር፤ የሔዋን ታሪክ የሚነግረን የሚከተለውን ነው፡ ‹‹ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤›› ዘፍ. 3
የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ማለት ‹‹እንደእግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ›› ሆኑ ማለት ነው፤ አሁንም ሔዋን መስከረምና ባለመጽሐፉ እንዳቀለሏት አለመሆንዋን መረዳት ይቻል ነበር፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል! በአንጻሩ አዳም የፍርሃት አባት ነው፤ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤›› ያለው እሱ ነው! ስለዚህ ወይዘሮ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› የምትለውን በድላለችና ይቅርታ መጠየቅ ሳያስፈልጋት አይቀርም!
ሔዋን የተጠቀመችው ውጫዊ ገጽታን የሚያሽሞነሙን ሳይሆን የውስጥን የመንፈስ ኃይል ቆፍሮ በማውጣት ነበር፤ በዚህ የውስጥ ኃይል ለሚጠቀም ከውጭ ግፊት አይጠብቅም።
‹‹እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት›› አይወቀስም፤ ትላለች ወይዘሮ መስከረም፤ እየተገፉ የሚገኘው ባርነት ነው፤ እውቀት የሚገኘው በነጻነት ነው፤ መገፋት ከእውቀት ያርቃል እንጂ ወደእውቀት አያስቀርብም፤ የመስከረም ዋናው መልእክት ሰላቢውን እንጂ ሰለባውን አትውቀስ የሚል ነው፣ ወይም የኔ ሀሳብ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ዓይነት ሆኖባታል፤ ለመሆኑ ሰለባ የሚሆን ከሌለ ሰላቢ ይኖራል ወይ? ሰለባ ከመሆን በፊት ሰለባ ላለመሆን መጣር አንዱ የኑሮ ዓላማ አይሆንም ወይ? ከዚህ በፊት ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ደጋግሜ ጽፌ ነበር፤ ጭቆና የጨቋኙ ባሕርይ የሚሆነውን ያህል የተጨቋኙም ባሕርይ ይሆናል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የሚጠቅመውን ያህል ለተጨቋኙም ጭቆና ይጠቅመዋል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የኑሮው መሠረት የሆነውን ያህል ለሚርመሰመሱት የጨቋኝ ሎሌዎች ጭቆና የኑሮ መሠረታቸው ነው፤ እንዲህ እያለ ወርዶ ወርዶ የጭቆና ጠቃሚነት ለሎሌው ሎሌ፣ ለሎሌው ሎሌ ሎሌ … በኢትዮጵያ ምናልባትም የመጨረሻዋ የጭቆና ሰለባ ሚስት ትሆናለች፤ ወይም ልጆች ይሆናሉ! ጨቋኝና ተጨቋኝ የባሕርይ ቁርኝት አላቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ ወይዘሮ መስከረም ይህ እውነት ያልሆነበት ሁኔታ ወይም አጋጣሚ የምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤›› የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱትንና በቁማቸው የሞቱትን ሲያመሳስላቸው ነው! ለእኔ የሚታየኝ እንዲህ ነው።
መስከረም ብዙ ታላላቅ ሴቶችን ጠቅሳለች፤ በእስዋ ግምት ሁሉም በአባታቸው ወይም በባላቸው እየተገፉ ወደትልቅነት መድረኩ የወጡ ናቸው፤ አዙራ ብታየው የጠቀሰቻቸውን ሴቶች ገፉ የምትላቸው ወንዶች መጀመሪያውኑ በሴቶቹ ተገፍተው እንደነበረስ ሊታሰብ አይገባም? ምናልባት ከጠቀሰቻቸው ሴቶች ይልቅ መስከረም የሄለን ኬለርን ታሪክ ብታስታውስ ኖሮ መገፋትን አታነሣም ነበር፤ ሄለን ኬለር በሕጻንነትዋ ዓይኖችዋም ጆሮዎችዋም ሥራቸውን አቆሙ፤ የሄለን ኬለር የመንፈስ ጥንካሬ ከውስጥዋ አዲስና የተሻሉ ዓይኖችንና ጆሮዎችን እንድታበቅልና እንድትማር፣ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያዋ ሴት ምሩቅ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል፤ ይህች አስደናቂ ሴት ከመቶ ሠላሳ ዓመታት ግድም በፊት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የነበረውን አጥር ሰብራ፣ ዓይኖችዋ ባለማየታቸውና ጆሮዎችዋ ባለመስማታቸው የገጠማትን እክል አሸንፋ ራስዋን ከወንዶች በላይ ለማድረግ በቅታለች።
መገፋትን የሚፈልግ ሁሉ፣ ካልገፉት የማይነቃነቅ ሁሉ፣ ሬትን ሲግቱት ይጣፍጣል እያለ የተቀበለ ሁሉ፣ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ፣ እያሉ አታልለው እንኳን ዶሮ የለም ሹሮ ሲሉት የማይናደድ ሁሉ፣ ምኞቱ ልደግ ልመንደግ እያለ ሲነዘንዘው በአፈና ጭጭ የሚል ሁሉ ለወቀሳ ብቻ አይደለም ለውርደትም ክፍት ነው፤ ስለዚህም ተወቅሶ ከውርደት ከዳነ ወቀሳው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፤ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጆች ሁሉ — ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ-አሮጊት፣ ባለሥልጣን ተራ፣ ገበሬ ነጋዴ፣ ወታደር ፖሊስ፣ አስተማሪ አስተዳዳሪ፣ ዳኛ ጠበቃ፣ ሀኪም መሀንዲስ፣ … — የፈለገውን ቢሆን ላለበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የራሱና የግሉ ነው፤ ራሱን የሚገነባው ወይም ራሱን የሚንደው ራሱ ነው፤ ሰበብ እየፈለጉ ከዚህ ኃላፊነት መውጣት ቀላል ቢመስልም ተመልሶ እምቦጭ ነው፤ ዳገቱን ለመውጣት የሚመረውን እውነት መቀበል ያሻል።
በመጨረሻም በማናቸውም መንገድ፣ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ወደቁልቁለት የሚገፉትን ወይም የሚነዱትን ‹‹እምቢ!›› ብሎ ድምጹን ያላሰማ ገደል ገብቶ ሲንፈራፈር ከራሱ በቀር የሚወቅሰው የለም፤ አቅመ-ቢስነት ከውጭ አይመጣም።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ በኖርዌይ ኦስሎ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ April 14, 2014

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11826/

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ
Ginbot7 meeting in Norway
በዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ  የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አዘጋጅነት አፕሪል ቅዳሜ 12/2014  በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ  የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሄደ:: በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከኦስሎ እና ከተለያየ ከተማ በመምጣት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን  የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል::
ሕዝባዊ ስብሠባው በኖሬጅያውያን የሰአተ አቆጣጠር ከቀኑ 15:00 እስከ ምሽቱ 21:00 ሰዓት የተካሄደ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አቢ አማረ በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አረመናዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ አስር ቤቶች በፖለቲካ ኣስተሳስባችው ምክንያት ያለወንጀላች የሚስቃዩ ውድ ኢትዮጵያዊን ወገኖቻችን በማስብ  በዚሁ ዘረኛ ቡድን አስቃቂ የኣካል ጉዳት ለተፈጸባቸው ኢትዮጵያዊን  የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማስደረግ ስብሰባውን አስጀምረውታል::
በመቀጠለም አቶ ዮሀንስ አለሙ የዴምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ስለ ዲምክራሲያዌ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አመሰራረት እና ስለ ድጋፍ ድርጅቱ አላማ በማብራራት የድጋፍ ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት በሀገር ቤት በሰላማዊ ትግል የወያኔን መንግስት ለመጣል እየታገሉ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶችን እየረዳ እንደሚገኝ እና ከሀገር ውጭ ደግሞ የወያኔን መንግስት  በሁለገብ ትግል  ለማስወገድ እየሰራ ያለውን የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅትን በግንባር ቀደምነት እየረዳ እንዳለ በመግለጽ  የወያኔን ዘረኛ ስርአት ለመጣል ሁሉም ሰው አስተዋጿ ማድረግ እንደሚጠበቅበት እና ማንኛውም  ኢትዮጵያዌ ዜጋ በሀገራችን የጋራ ጉዳይ ስለሆነው  የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሀሳብ በመለዋወጥ ፣በመካከላችን ያሉትን ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ኋላ በመጣል ፣ በመቻቻል፣ ሀገር እያፈረሰ እና ሕዝብ እያዋረደ ያለውን የዘረኛውን የወያኔን መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁለገብ ትግል ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበት አጽኖት ሰጥተው ንግግር አድርገዋል::
Ethiopians public meeting in Norway
በመቀጠለም ዲምክራሲያዊ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል የሆኑት አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ ሰፊውን ጊዜ በመውሰድ ከንጉሱ ስርአት ጀምሮ በደርግ መንግስት ዘመንም በሀገራችን የተደረጉ የፖለቲካ ንቅናቄዎችንና ለውጦችን አንድ በአንድ በመዘርዘር አሁን ካለው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ጋር በማነጻጸር ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ላይ ሀገሪቱን እየመራው ነው የሚለው የወያኔ መንግስት ከዚህ ቀድሞ ኢትዮጵያን ከመሩት ከሁለቱ መንግስታቶች ማለትም ከንጉሱም ከደርግም መንግስት ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ እንደማይገናኝ የወያኔ መንግስት ዘረኛና የዘረኝነት ፖለቲካ እያራመደ ያለ አረመናዊ መንግስት እንደሆነ አብራርተዋል::
የግንቦት 7  የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ አክለውም ከወያኔ በፊት የነበሩ ሁለቱ መንግስታቶች ለውድቀት የዳረጓቸውን ምክንያቶች በመጥቀስ የወያኔን አንባ ገነናዊ መንግስት ለአፋጣኝ ውድቀት ሊዳርጉት ይችላሉ የሚሉትን ግልጽ ምክንያቶች በመዘርዘር አስቀምጠዋል:: አቶ ቡዙነህ በሁለት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማንሳት እና በማብራራ ከሕዝብ ውይይት እንዲያደርጉበት ለመወያያ ያቀረቡ ሲሆን እነዚህም:
1, በሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በወያኔ መካከል ያለው ግጭት
2, የህዳሴ ግድብን  በማስመልከት ያለው ተቃውሞ
ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሲናገሩ የሙስሊሙ ትግል በሁለት አመታት ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ትግል በጣም የተሳካና ወያኔ በቀላሉ ሊያዳፍነው ያልቻለው ሰላማዊ መብትን የመጠየቅ ትግል እንደሚያደንቁ በመናገር ነገር ይህ በሙስሊም ማህበረሰብ በኩል እየተደረገ ያለው ትግል እስከ አሁን ድረስ ከመንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ሊያገኝ እንዳልቻለ እና ወደፊትም ከወያኔ መንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል:: ለዚህም ማስረጃው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከጠየቋቸው አራት የመብት ጥያቄዎች አንዱም ካለመመለሱ በተጨማሪ እስካሁን መሪዎቻቸውም በሃሰት ውንጀላ በእስር እየማቀቁ ያለፍርድ እየተንገላቱ መሆናቸው ነው::
ነገር ገን አሁን እየሆነው ባለው ሁኔታ በእንደዚህ አይነት መንገድ እስከመቼ ድረስ የሙስሌሙ ትግል ይቀጥላል በማለት የተናገሩ ሲሆን አሁን እየሄደ ባለው አካሄድ የሙስሊሙ ተቃውሞ የትግል አቅጣጫውን እስካልቀየረ ድረስ ረጅም ርቀትን ትግሉ ሊቀጥል ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ነግር ግን የሙስሊሙ ጥያቄ ከእምነት መብት ጥያቄ ባሻገር ወደ የዜግነትን መብት ወደ ማስከበር መለወጥና መሸጋገር  እናደለበት በመናገር የሙስሊሙ ማእበረሰብ ጥያቄ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው  ትግሉ በዚህ መልኩ ሲቀጥል እንደሆነ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰተዋል::
በሁለተኛም የህዳሴ ግድብ በሚመለከት  ያቀረቡት ሀሳብ ወያኔ የራሱን የፖለቲካ ኪሳራና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ በዕድገት ስም ለመሸፈን ያመጣዉ እንጂ ታቅዶበትና ለህዝቡ በማሰብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉ ግፍ እንደ ማስረጃነት በማቅረብ ያብራሩ ሲሆን እንደ ምሳሌም ወያኔ ሃገራዊ የሆነ አላማ ይዞ ካለመነሳቱ አንፃር የሃገርን ድንበር አሳልፎ እስከመስጠት እየሄደ ያለበትን ሁኔታ ጠቅሰው ይህ አሰራር ደግሞ የዲክታተሮች ባህሪ እንደሆነ አብራርተዋል::
የወያኔ መንግስት በህዳሴ ግድብ ሰበብ ምክንያት በማድረግ በመላው አለም ኢትዮጵያኖች በሚኖሩበት ሀገሮች በመዞር የዲያስፖራውን ቀልብ ለመውሰድ የሚያደርገው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ሩጫ በዲያስፖራ ተቃዋሚዎች አማካኝነት በፍጹም እንዳልተሳካለት ይህንንም የወያኔ በአባይ ቦንድ ሽያጭ ስም ገንዘብ ዘረፋ በመቃወም ወያኔን አሳፍረው ከመለሱት መካከል በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እንደሆኑ በማስታወስ  የዚህ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰበብ የወያኔን መንግስት ወደ መጥፎ ውድቀት ላይ ሊጥለው እንደሚችል በማመን የወያኔ መንግስት በአሁን ሰአት ከግብጽ መንግስት ጋር እየገባ ያለው ሰጣ ገባ ለኢትዮጵያ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃለዋል::
በመቀጠልም አቶ ብዙነህ ባነሷቸው ነጥቦችና እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰፋ ያለ ውይይትም ተደርጓል፥፥ ከውይይቱም በማስቀጠል የዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንሄል አበበ የዲምክራሲያዌ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የአቋም መግለጫ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ድርጅታቸው ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ፈጽመው እንደሚያወግዙ እና ዴምክራሲያዌ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሁል ጊዜ ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ ጎን እንደሚቆም ቃል በመግባት የአቶ ቡዙነህ ፅጌን በኖርዌይ በመገኛት ለህዝቡ ለሰጡት ገለጻ አመስግነዋል::
በዝግጅቱ መጀመሪያና ማጠቃለያ ላይ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል መዝሙር በመዘምራን የተዘመረ ሲሆን በየጣልቃው የተለያዩ የባህል ዘፈኖች በተወዛዋዦች ታጅቦ የቀረበ ሲሆን ጣእም ያለው ባህላዊ ምግብም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የሴቶች ክፍል ተስተናግዷል፥፥ ስብሰባውን ተጀምሮ እስኪያልቅ አቶ ፍቅሬ አሰፋ መርተውታል::
በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላችሁን ላበረከታችሁና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች ረዥም ርቀት በመጓዝ የዝግጅቱ ታዳሚ ለነበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን እና እንዲሁም የድርጅቱ አባላቶች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ

በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብ በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ April 14, 2014

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11830/

Ethiopians demonstration in Norway
በ11-4-2014 በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብና ኖርዌ በስደተኛው ላይ ያላትን ፖሊሲ በመቃወም    የተቃውሞ ሰልፍ አረጉ።  23 ዓመት እራሱ መራጭ እራሱ ተመራጭ ሆኖ በጠመንጃ አፈሙዝ ህዝቡን እያንቀጠቀጠ የኖረው ወያኔ አንድ ቀን ሕዝብ በቃኝ ብሎ አንቅሮ እንደሚተፋውና ንብ ሆኖ ለነፃነቱ እንደሚነሳ ማወቅ ነበረበት።
ግን አልሆነም ዜጎች እንደዜጋ በሐገራቸው መኖር ቀርቶ በስደትም ሰላማቸውን ማግኘት አልቻሉም።
እስርና እንግልት፣ረሐብና ሰቆቃ፣ስደት የእያንዳንዱ እጣ ፋንታ ሆነ፤በወያኔ ዘመን ሰው ብቻ አይደለም መሬትም መሰደድ ጀምሮ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል የኢትዮዽያን ለም መሬት ለሱዳን በመሸጥ ላይ ይገኛል
ኢትዮዽያንና ኢትዽያዊነትን ያሉ ሁሉ አሸባሪ እየተባሉ በየእስርቤቱ ታጉረው እጣ ፈንታቸው እስርና እንግልት ሆነ ሐገራቸውን ጥለው በባሕርና በየብስ አቆራርጠው የሞተው ሞቶ የተረፈው በአለም ዙሪያ ተበትኖ ጥገኝነት  በመጠየቅ ይኖራል::
በዚሕም የተሳካላቸው ጥቂቶች ሲሆኑ ባብዛኛው ወያኔ ለውጩ አለማት በሚያሳየው ሁለተኛው ፊቱ ምክንያትና ምእራባውያን ከሐገሪቱ ከሚያገኙት ጥቅም የተነሳ ሐገርህ ዲምክራሲ ነው እየተባለ ፍትሀዊ ያልሆነ መልስ እየተሰጠው በመጉላላት ላይ ይገኛል።
ያም ሆኖ የሐገሩ ጉዳይ በደም ስሩ ሰርጎ የገባው ኢትዮዽያዊ ሁሉ ጠዋት ማታ ኢትዮዽያዬ እያለ ይጮሀል። ይህ የህዝብ ቁጣ ያስፈራው ወያኔ ያለ የሌለ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ እየመዘበረ ዜጎችን ይሰልላል ያሰልላል፣አልፎ ተርፎም ዜጎችን ከመሰሎቹ ጎረቤት ሐገሮች ድረስ በመሄድ ጎትተው እስርቤት ያስገባሉ።
ይህንን ለመቃወምና ለማውገዝ ነበር የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ኢትዮዽያውይኑ ዛሬም ስለ ሐገራቸው ሊጮሁ የወጡት፤ ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን እንዲህ በማለት ነበር ድምፃቸውን ያሰሙት እኛ ስደተኞች እንጅ ወንጀለኛ አይደለንም፣ኖርዌ ለማፊያው ወያኔ የምታደርጊውን እርዳታ አቁመሽ ከኢትዮዽያ ሕዝብ ጋር ቁሚ፣ወያኔ የሚያደርገውን ተግባር እናወግዛለን፣ሼም ኦን ዩ ሳውዝ ሱዳን ኦኬሎን አሳልፈሽ የሰጠሽ፣ወያኔ አሸባሪ ነው፣ለውጥ እንፈልጋለን፣ኖርዌ የዩኤንን ህግ ታክብር የሚሉትን የመሳሰሉ ሲሆን
በሰልፉ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮዽያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ተወካይ አቶ ዳንኤል የወያኔን ጀሌዎች የማጋለጡ ስራ በሚገባ እየተሰራበት መሆኑን ሲገልጡ ሰልፈኛው በጭብጨባ የተቀበላቸው ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም ተወካይ ኖርዌ ነፃ እንድታወጣን ሳይሆን ለወያኔ የምትሰጠውን እርዳታ አቁማ ድጋፍ እንድትሰጠን ነው፤ በተጨማሪም ኖርዌ አቶ ኦኬሎን ታስለቅቅ በማለት  ተጠይቃለች። በሰልፉ ላይ የኖርዌ ሊብራል ፓርቲ ተወካይ ከሰልፈኛው ደብዳቤ ተቀብለው መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኖዋስ ፣አንቲረሲስት ተወካዮችም እንዲሁ ይዘውት የመጡትን መልክት ለሰልፈኛው አስተላልፈዋል።
ከዚያ በቀጥታ ወደሶፊን በርግ ሎካል አዳራሽ ሰልፈኛው አምርቶ ምሳ  ከተበላ በሁዋላ ኮሚቴው ካባላቱ ጋር ሰፊ ዉይይት ያደረገ ሲሆን የ፫ወር የስራ ሪፖርትም አቅርቦአል።
የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ