Monday, April 4, 2016

እውን በኢትዮጵያ ውስጥ ‘’ነፃነት’’ አለን!?!


ዳንኤል ፍቅሬ

የሕወሓት አገዛዝን በመደገፍ አሊያም በመተባበር ብቻ ነፃነት አለ፡፡ ህወሓት በፈለገው ሰዓት የፈለገውን አጀንዳ ቀርፆ ድጋፍ እንዲደረግለት በግዳጅና በአነስተኛ የውሎ አበል ክፍያ ሰልፍ በመውጣት “ነፃነት” አለ፡፡
አገዛዙን በመተቸት እና ስለህዝቡና ስለ ሀገራችን ያገባናል በሚል የሕወሓትን ብልሹ አሰራር የተቃወሙትን እስር በመደገፍ በየቀበሌውና በየአዳራሹ ተስብስቦ እስሩን በመደገፍ “ነፃነት” አለ፡፡ የአገዛዙ ጠብደል ሹማምንት የህዝቡን እና የሀገሪቱን ጥቅም ያለ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት ሲፈልጉ እንዳሻቸው አሊያም ለሌላ ሶስተኛ አካል በፍላጎታቸው ልክ ሲቸሩ ዝም በማለት “ነፃነት” አለ፡፡
የሕወሓትን ድርጊት ለመደገፍ አሊያም በዝምታ በማለፍ “የፕሬስ ነፃነት” አለ፡፡ ይሄ ነው የዛሬዋ የሕወሓቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ፍትህ እና ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፡፡ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ ለመቃወምና ለማጋለጥ፣ የተሻለ አማራጭ ሐሳብ ማንሳት፣ ዜጎች ሌላው ሰው ሳይጎዳ ያመኑበት እና የመረጡት ሐሳብ ማንሳት አሊያም ማራመድ፣ ለሀገርና ለወገን መቆረቆር እንደወንጀል ተቆጥሮ በሐሰት ክስ በሕወሓት አሰቃቂ ማጎሪያዎችና የካንጋሮ ፍርድ ቤት ለመንከራተት ተገደዋል።

አዎ! ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ትግበራ መቆም፣ ለዜጎችና ለሀገሪቱ ጥቅም መቆርቆር፣ የአገዛዙን ህገ-ወጥ ተግባራት መቃወም፤ የሕወሓት ወንጀለኛ ሹማምንትን ፍላጎት ለማርካት ሲባል ብቻ ሰው የመሆን ማንነት ተፈጥሮን የሚፈታተን በደል ከማስተናገድ አልፎ በየወህኒ ቤቱ ግፍ እስር እየተሰቃዩ ያሉ ዜጎችን ቤት ይቁጠራቸው። በነገራችን ላይ ባለፉት 25 የሰቆቃ ዓመታት በሕወሓት አገዛዝ ከተፈፀሙት የግፍ እስር፣ እንግልትና ስቃይ ውስጥ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች፣ ፖለቲከኞች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ገበሬዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ነፃነት ጠያቂዎች፣… ወዘተ ይገኙበታል፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ እስሩ፤ ግድያው፤ ሰቆቃው በሕወሓት አገዛዝ እየተፈፀመ ያለው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ ዘር፤ ፆታ፤ ሀይማኖት፤ የሙያ ዘርፍ ሳይለይ ነውና ሁላችንም በጋራ ይህንን ነፍሰ ገዳይ ቡድን ‘’በቃ!’’ በማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአገራችንን ምድርና ከህዝባችን ጫንቃ ነቅለን ለማስወገድ በጋራና በአንድነት ልንነሳ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሰዓቱ አሁን ነው!!! አለያ የባርነት ቀንበር ተሸክመን ለተጨማሪ የስቃይና የሰቆቃ ዓመታትን ለመጋፈጥ እንገደዳለን!!


ፍትህ፣ ነፃነት እና እኩልነት ለሁሉም ዜጎች!!

#Free All Prisoners Of Conscience! #Free Journalists! #Free Bloggers!#FreePoliticians! #FreeEthiopia!