Thursday, August 17, 2017

ሕዝባዊ ትግሉና ዲያስፖራው

ሕዝባዊ ትግል ወይም አመጽ ወሳኝ የትግል ስልት መሆን እንደሚችል ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን እያካሄዱት ያሉት ትግል ጥሩ ማስረጃ ነው። ትግሉ እስካሁን ድረስ ከተገመተው በላይ በርካታ ድሎችን አስገኝቷል። ቀጥለው የተዘረዘሩትን ዋና ዋና ክስተቶች  የትግሉ ውጤት እንደሆኑ መናገር ይቻላል። አንደኛ መንግስት ሊተገብራቸው ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች ለጊዜውም ቢሆን በሕዝብ ትግል የተነሳ እንዲቆሙ አድርጓል። ሁለተኛ ትግሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ አድርጓል። ሦስተኛ የክልል ባለ ሥልጣናት በተወሰነ መልኩ ሕወሓትን እንዲገዳደሩ የሞራል ተነሳሽነት ሰጥቷል። 


አራተኛ ከፍተኛ የፌዴራል የመንግስት ባለ ሥልጣናት ከምንም ጊዜ በላይ እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል። አምስተኛ ውጥረቱን ለማስተንፈስ  በሚመስል መልኩ መካከለኛና ዝቅተኛ ባለ ሥልጣናትና ካድሬዎች ከሥራ እንዲባረሩ ትግሉ ምክንያት ሆኗል። ብዙዎችም በስርቆት ክስ ዘብጥያ እንዲወርዱ ምክንያት ሆኗል። ስድስተኛ አገዛዙ ከሕዝብ ሊሰበስበው የነበረው የገቢ ግብር በታቀደው መሠረት እንዳይሰበሰብ አድርጓል። ሰባተኛ ሕዝባዊ ትግሉን ለመግታትና ለማቆም  መንግስት በወሰደው አረመናዊ ጭፍጨፋ የተነሳ እርዳታ የሚለግሱት የውጭ አካላት የአገዛዙን ማንነት ይበልጥ እንዲረዱ ፖሊሲያቸውንም እንደገና እንዲፈትሹ አድርጓል። ስምንተኛ ምንም እንኳን ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ቢከፈልበትም ሕዝብ በእምቢታው ከቀጠለ መንግስትን ማንበርከክ እንደሚችል የማይረሳ ትምህርትና ተሞክሮ ተገኝቷል። ለዚህም ነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጌዜ እንኳ ሳይቀር ትግሉ ሊቀጥል የቻለው! በመሆኑም እስካሁን ድረስ የተካሄደው ትግል እጅግ በብዙ መልኩ ውጤታማ እንደሆነ መንግስት ሳይቀር ሊቀበለው የሚገባ ሐቅ ነው።              

ዳሩ ግን ትግሉ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ ወይም መንግስት ሙሉ በሙሉ  ሥልጣኑን ለሕዝብ እንዲያስረክብ አላደረገውም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። አንደኛ ትግሉ በፈረቃ መካሄዱ  መንግስት ኃይሉን እያጠናከረ ሕዝቡን እንዲደፍቅ እድል ፈጥሮለታል። የሙስሊሞች ትግል፣ በኦሮሚያ የሚካሄደው ትግል ከዚያም የአማራው ትግል በሂደትና በተለያዩ ጊዜያት የመጡና ያልተቀናጁ ናቸው። አሁንም ቢሆን አመጹ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት እየተካሄደ ይገኛል። ይህ ፈረቃዊ ትግል የመንግስት ወታደሮች ከቦታ ቦታ እየተስፈነጠሩ እንዲመቱት አስችሏል። ሁለተኛ ትግሉ በፈረቃና ያለ ቅንጅት  የሚካሄደው ወጥ አመራር ስለሌለው ነው። ትግል  መሪን ይወልዳል እንዲሉ በሂደቱ ከፊት የተሰለፉ  ጀግኖች ብቅ ብለው ነበር። ይሁንና ሳይውሉ ሳያድሩ ምህረት የሌለው የካድሬ በትር አርፎባቸዋል። ብዙዎች በመንግስት ኃይሎች ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ በሽተኞች ተደርገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ወገባቸውን ተመተው በመኖርና ባለመኖር መካከል እያጣጣሩ ይገኛሉ። ይህን ሁሉ በማድረግ ግን መንግስት ውጤታማ እንደሆነ መናገር ይቻላል! ሦስተኛ በቂና የተቀናጀ  ደጀንና ድጋፍ የለም። ትግሉን የሚያካሂደው ሕዝብ እርሻውንና ንግዱን ትምህርቱንም ትቶ በራሱና በቤተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ፈርዶ  ነው። ይህ አይነት ትግል ፍጥነትና ዘለቄታዊ ውጤት የሚያመጣው ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲኖር ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ትግሉ መቀጠሉ የሕዝቡን የብሶት መጠን ከማሳየቱም በላይ ሕዝብና መንግስት ዳግም ላይገናኙ በይፋ ፍቺ መፈጸማቸውን ያበስራል።    
             
የዲያስፖራው እንቅስቃሴ

ኢትዮጵያዊው ዲያስፖራ (በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና የሲቪክ ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃንና  ግለሰቦች) በበኩሉ አገር ቤት ትግሉ በሚካሄድበት ወቅት የራሱን አስተዋጽዖዎች ሲያደርግ ቆይቷል። ቀጥለው የተዘረዘሩት ጎላ ብለው የታዩ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል። ይህ ማለት ግን እነዚህ እንቅስቃሴዎች በሕዝባዊ ትግሉ አማካኝነት የተከናወኑ ናቸው ማለት አይደለም። ትግሉ በሚካሄድበት ወቅት አብረው በመከሰታቸው ከትግሉ እንቅስቃሴ ጋር ቢወሱ ክፋት የለውም። እንዲያውም በርካታ እንቅስቃሴዎች ትግሉን በተለያዩ  መንገዶች ለመደገፍ ያለሙ ናቸው። 
  • በረሃ ያሉ የትጥቅ ትግሎች ከበፊቱ የተለየ እንቅስቃሴ አድርገዋል። እንደ ድርጅቶቹ መግለጫዎች ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ወታደሮቻቸውን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ችለዋል። እንዲያውም ከአገዛዙ ኃይሎችና መገለጫዎች ጋር ፍልሚያ እንደጀመሩም  አሳውቀዋል። ይህ በራሱ በቀጣይነት ለሚደረግ ትግል ወሳኝ ስለሆነ በራሱ እንደ ድል ሊቆጠር ይችላል። አገር ቤት ሆኖ ለሚታገለው ሕዝብም ሞራልና ተስፋ ሊሆን ይችላል
  • ምንም እንኳን የድርጅቶቹ አቅምና ቁመና ገና በግልጽ ባይታወቅም አራት ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ምስረታም አንድ እርምጃ  ነው። ብሄራዊ አደረጃጀትንና አጀንዳን ሊያጠናክር ይችላል 
  • በቪዥን ኢትዮጵያ አነሳሽነት ዕውቀትና ጥበብ የፈሰሰባቸው ታላላቅ ኢትዮጵያ አቀፍ ጉባኤዎች ተካሂደዋል። ለብሄራዊ እርቅና መግባባት እንዲሁም ባጠቃላይ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች ተሰብስበዋል። የበለጠ መተዋወቅ እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ በጋራ የጋራ ብሄራዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መለየት እንደሚቻል ትምህርት አስተላልፏል
  • 17 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ጉባኤ ተመስርቷል። እንደ ጉባኤው የአቋም መግለጫ ከሆነ ይህ ኮሚቴ «የሽግግር ሂደት ሊመራ የሚችል፤ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ምክርቤት በአጭር ጊዜ ለመመሥረት የሚያስችል ጥናት የሚያደርግ፤ ከሌሎች ተመሳሳይ ጥረት ከሚያደርጉ ወገኖች ጋር በቅንጅት የሚሰራና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባኤ ቀጣይነት ባለው መልኩ በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች እንዲደረግ” ያስተባብራል። ይህም በራሱ መልካም ጅምር ነው
  • የኦሮሞውን ማኅበረሰብ በማስተባበርና በማደራጀት በኩል የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎክ ከፍተኛ የሚባል ሥራ አከናውኗል። በኦሮሚያ አካባቢዎች የተካሄዱትን ትግሎች ለዓለም አስተላልፏል።  የመንግስትን ብልሹ አሠራሮች አጋልጧል
  • የአማራውን ማኅበረሰብ ለመታደግ ደግሞ በአጭር ጊዜ እንደ እንጉዳይ የፈነዱ ንቅናቄዎች ድርጅቶች ተፈጥረዋል። ምንም እንኳን እርስ  በርሳቸው መናበብ ባይችሉም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ዳሩ ግን የአማራው መደራጀት እንደ ሌሎች ብሄር ተኮር ድርጅቶች በቀላሉ ተቀብሎት ባለማግኘቱ ቀላል የማይባል ክርክርና ውይይት ተካሂዷል
  • ኢትዮጵያ ተኮር ድረ ገጾችም ዜናዎችን ከመዘገብ በተጨማሪ ውይይቶችን በማነሳሳትና በማሰራጨት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል   
  •  ምናልባትም ከነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች እጅግ በላቀ ደረጃ ትግል ያደረገ ተቋም ቢኖር ኢሳት ነው። የአገር ቤቱን ትግል በትኩሱ ከመዘገቡም በላይ ምሁራንንና የተቋማት አመራሮችን እንዲሁም ግለሰቦችን በመጋበዝ ታሪካዊ ሥራ አከናውኗል። ኢትዮጵያዊያን መንግስት የሚያደርሰውን አድሎ፣ ሙስናና ዘረኝነት በተጨባጭ እንዲገነዙ አድርጓል። ለመንግስት ከፍተኛ የራስ ምታት ሆኖበታል። ኢሳትን ለማፈን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥቷል። ላለማጋነን ከሁሉም የዲያስፖራ ትግሎች መንግስትን በእጅጉ ያሸበረውና የተገዳደረው ኢሳት ነው!    
ከዚህ ባለፈ በውጭው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ የተበታተኑ የገንዘብ፣ የሞራልና የዲፕሎማሲ ድጋፎችንም ለማቅረብ ሞክሯል። ባጠቃላይ ሲታይ ግን ከኢሳትና ከሌሎች ሚዲያዎች  በስተቀር ዲያስፖራው ለሕዝባዊ ትግሉ በቀጥታ ያበረከተው አስተዋጽዖ እምብዛም አይደለም። እንዲያውም ምስኪን ኢትዮጵያዊያን በየቀኑ መስዋዕት እየሆኑ በዲያስፖራው የሚካሄዱት አንዳንድ ውይይቶችና ክርክሮች ለትግሉ የማይረባ ከመሆናቸውም በላይ አገር ቤት ያለውን ኢትዮጵያዊ ግራ አጋብቷል ለማለት ይቻላል።  ዲያስፖራው ካለው ምቹ ሁኔታ አኳያ ሊያደርገው የሚገባውን  አላደረገም።   

የዲያስፖራው ፈተናዎች

ዲያስፖራው እጅግ ብዙ ፖለቲካዊና ሲቪክ ተቋማት እያሉት ለምንድን ነው የተቀናጀና ትርጉም ያለው ድጋፍ ሳያደርግ የቀረው? በርካታ ቀጥታዊና ኢ-ቀጥታዊ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል።  
  • የተወሰኑት ድርጅት እንደሆኑ ቢናገሩም ገና የድርጅት አቅምና ባህርይ የላቸውም። በማኀበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገዝፈው ቢታዩም መሬት የነካ እንቅስቃሴ የላቸውም! የጥቂት ግለሰቦች ብቻ  መድረክ የሆኑ አሉ
  • በዲያስፖራው ስም ተቃዋሚ እንደሆኑ ቢናገሩም ተቃዋሚ ያልሆኑም አሉ። እንዲያውም የዲያስፖራውን ትግል የሚያቀጭጩ በስውርም መረጃ ለመንግስት የሚቀልቡ እንዳሉ ይታመናል
  • ቀላል ቁጥር የሌላቸው ድርጅቶች ደግሞ በአንድ ወቅት ካዘጋጁት የድርጅታቸው መርሐ ግብር ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳለ አይቀበሉም። የትግል ግብና ዓላማ ስልት ሳይቀር እነሱ ካስቀመጡት የተለየ ከሆነ ለትብብር በራቸው ዝግ ነው። ይህም አልፎ ሌሎችንም ለማደናቀፍ በተለያዩ መንገዶች የሚንቀሳቀሱ ይኖራሉ
  • ሰላማዊና ሁለ ገብ የትግል ስልቶችን  የመረጡት ድርጅቶች የትጥቅ ስልትን ከመረጡ ድርጅቶች ጋር ለመናበብና ለመሥራት አይፈልጉም። በሽብርተኝነት እንዳይፈረጁም ይሰጋሉ! እንዲሁም  ቋንቋንና ዘርን መሠረት ያደረገና ብሄራዊ አስተሳሰብን መነሻው ያደረገ አደረጃጀት ለትብብር ቀርቶ ለሰከነ ውይይትም አላበቃም። አገር ቤት የንጹሃን ደም በየቀኑ በወታደር እየፈሰሰ ዲያስፖራው የሚከራከረው በዘር ስለመደራጀትና አለመደራጀት ነበር። አንዱ ሌላውን በተቃርኖ አስቀምጦታል
  • የግል አጀንዳ ወይም ጥቅም ይዘው የሚንቀሳቀሱ አባላት እንደሌሉ ማሰብም የዋህነት ነው
  • የአባላት የአቅም ሁኔታም ሌላው እንቅፋት ነው! ሕዝባቸውን ለማገልገል ፍላጎት ቢኖራቸውም እንዴት መንቀሳቀስና መተባበር እንዳለባቸው ብዙም የማይረዱ አሉ። ስሜት እንጅ አቅም የሌላቸው የድርጅት ሓላፊዎች፣ ጸሐፊዎችና ግንኙነት  ክፍሎችን ማየት አዲስ ጉዳይ አይደለም
  • ዕውቀቱና ተሞክሮው ያላቸው ደግሞ ለትናንት ታሪካቸው እስረኛ ሆነው ይስተዋላሉ። በጃንሆይና በደርግ በኋላም በወያኔ ዘመናት በተለያይ የፖለቲካ ትግሎች የሚተዋወቁ አብዝተውም የሚተቻቹ ሞልተዋል። እነዚህ ሰዎች አይደለም አብረው ሊሠሩ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለመሄድ ብዙም አይገዳቸውም
  • አብዛኛው ዲያስፖራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያካሂደው በትርፍ ጊዜ ነው። አድካሚ ከሆነ ሙሉ ሥራና ከቤተሰብ የተረፈ ቅንጭብጫቢ ጊዜ ነው ለፖለቲካ ሥራ የሚመደበው! ይህ ደግሞ  እጅግ የታሰበበት አዋጭ ሥራ እንዳይታቀድና እንዳይከናወን እያደረገ ነው  
  • ብዙ ሊባሉ የሚችሉ የድርጅት አመራሮች በዝምድናና በትውውቅ የተሳሰሩ ናቸው። ይህም ከራሳቸው ምቹና ስጋት የሌለው ከሚመስል አሠራር ወጥተው ከሌሎች ጋር አጥጋቢ ትብብርን እንዳያደርጉ ያደርጋል። ይህ አሠራር ለግልጽነትና ተጠያቂነትም አይመችም  
  • ዲያስፖራው በሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር የተከፋፈለ ነው። ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በስውርና በይፋ መንግስትን የሚደግፉ አሉ። እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሲኖዶስ ስር ያለ ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያን ሁሉ የወያኔ፣ ውጭ ባለው ሲኖዶስ ስር ያሉ ሁሉ ደግሞ የተቃዋሚ ጎራ ተደርገው ይታያሉ። ይህ ሾላ በድፍን የሆነ አስተሳሰብ አንድነትና መናበብ እንዳይኖር የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል
  • ብዙ ድርጅቶች ውሳኔ አሰጣጣቸው እንደ ቀድሞው አሠራር ከላይ ወደ ታች  ነው። ከፍተኛ አመራሮች በራቸውን ዘግተው ይወስናሉ።  መካከለኛና ዝቅተኛ አማራሮች እንዲሁም አባላት ደግሞ  ውሳኔችን የመፈጸም የውዴታ ግዴታ አለባቸው። በሕዝባዊ ውይይት ስም ጉባኤ ተጠርቶ መግለጫና ማስታወቂያ ብቻ አሰምቶ መሄድ የተለመደ ነው። ይህ አይነት የሥራ ባህል አባላት የባለቤትነት ስሜትና የሥራ መነቃቃት እንዳይኖራቸው ከማድረጉም በላይ ያላቸውን አማራጭ ተሞክሮዎች  በውይይት አዳብረው እንዳይጠቀሙ ይገድባል። በቆይታም እቅዶች በአግባቡ ሳይፈጸሙ ይቀራሉ። ይህም በአባላት ዘንድ መሰላቸትና ከትግል መራቅን ያስከትላል                      
በአጠቃላይ ሲታይ ዲያስፖራው ካለው እምቅ አቅም አኳያ ሲታይ ለሕዝባዊው ትግሉ እምብዛም ድጋፍና ደጀን ሊሆን አልቻለም። ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነም በዲያስፖራውና አገር ቤት ባለው ኢትዮጵያዊ መካከል ያለው የሥራ ግንኙነት ፈጽሞ ሊቋረጥ ይችላል። በመሆኑም ዲያስፖራው ሰከን ብሎ ለመራመድ ይችል ዘንድ አሠራሩንና  ግቡን መፈተሽ ይኖርበታል። ለግል ጥቅምና ዝና የሚቋምጡ፣ የዲያስፖራውን ትግል በተለያዩ መንገዶች ከውስጥ ሆነው የሚያቀዘቅዙ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚፈሩ፣ በ60ዎቹና በ70ዎቹ ታሪክና ፖለቲካ የሚቆዝሙ፣ ባጠቃላይ ወቅታዊና የዴሞክራሲያዊ አሠራር ባህል የማይዋጥላቸውን ከአመራር ቦታዎች ሊነሱ ይገባል። በአንጻሩም የራሳቸውን ድርጅት ብቻ በማፍቀር ሌሎችን የሚቃወሙ መንግስትን ካልሆነ በስተቀር ማንንም እየጠቀሙ እንዳልሆነ ይረዱ። በትውውቅ በዘፈቀደና በስሜት የሚደረግ ሥራ መቆም ይኖርበታል። ልዩነትን አቻችሎ መናበብን ከዚያም መተባበርን መልመድ ከምን ጊዜውም በላይ አሁን ያስፈልጋል።  

ማጠቃለያ

ዲያስፖራው ከላይ የተዘረዘሩት ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም በአገሩ ጉዳይ ከማሰብና ከመጨነቅ ብሎም የሚቻለውን ከማድረግ አልቦዘነም። ለዚህም ምስጋናና እውቅና ያስፈልጋል! ይሁንና ውጤት ለማምጣት  ከተፈለገ ትግሉ በብዛትም በጥራትም ተጠናክሮ ሊመራ ያስፈልገዋል። የተናጥል እንቅስቃሴዎች የትም አያደርሱንምና ቅንጅትና መናበብ ያስፈልጋል። 


እስካሁን ድረስ እንደታዘብነው ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ፍጹም ውህደት እንዲፈጥሩ መጠበቅ የሚከብድ ይመስላል። ያለው ብቸኛ አማራጭ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን ምንነትና ማንነት እንደያዘ የጋራ ፕሮጀክቶችን መንደፍ ነው። ይህም ማለት ድርጅቶች ስማቸውንና የራሳቸውን ፕሮግራም እንደያዙ በጋራ ሊሠሯቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አብሮ መለየትና መሥራት ነው። ሁሉም ድርጅት ባይቻል አብዛኛው ተገናኝቶ  መወያየትና ሁሉንም የሚወክል አስተባባሪ ግብረ ኃይል ማቋቋም ወሳኝ ነው። ከዚህ በፊት የተመሰረቱት አገራዊ ማለትም ብሄራዊ ንቅናቄዎች ይበልጥ ግልጽነትን፣ ሁሉን አሳታፊነትንና ተጠያቂነትንም አዳብረው ሊወጡት የሚችሉት ታላቅ ሓላፊነት ነው። ያለበለዚያ በተናጥል የሚደረግ ትግል ተሳተፍን ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈይደው ጉዳይ አይኖርም። 
          
በዶክተር ተክሉ አባተ