Thursday, March 8, 2018

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ኦህዴድ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ናቸው። የቀድሞው አምባሳደር ያማማቶ ስለለውጥ ያወራሉ። የትግራይ ገዢ ቡድን የአሜሪካን ባለስልጣናት እግራቸው የአዲስ አበባን መሬት መርገጡን ተከትሎ በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት የቀለም አብዮት ላይ አካኪ ዘራፍ እያለ ነው። ለመጪው ዕሁድ የተጠራው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምክርቤት ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እስከመኖሩም የዘነጋው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራዩን አገዛዝ አረፋ እያስደፈቀ ማንደፋደፉን ቀጥሎበታል። ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም። ይሮጣል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድብን ካለ ድብታ፡ ድንዛዜና ሰመመን ወጥቶ በብርሃን ፍጥነት ወደ ለውጥ እየገሰገሰ ነው። ጥያቄው ምን ዓይነት ለውጥ ይሆናል የሚለው ነው። ወደተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ልግባ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጥቅል የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የታወጀ የሞት አዋጅ ቢሆንም በተናጠል ያነጣጠረው ኦህዴድ ላይ ነው። መቀሌ ላይ ለሁለት ወራት ተጎልተው መርዝ ሲቀምሙ የከረሙት የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት መርዛቸውን ሸክፈው፡ ጓዛቸውን ጠቅለለው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የጠበቃቸው የሙክታር ዓይነቱ ተላላኪው ኦህዴድ አለነበረም። በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ በስልክ መሪውን የሚቀይሩት የአባዱላ ገመዳ አደርባዩ ኦህዴድም አልነበረም። ሰለሞን ጢሞ የተሰኘው የትግራይ ገዢ ቡድን አመራር እንደፈለገው የሚያሽከረክረው የኩማ ደምቅሳ ኦህዴድም አይደለም። ይልቅስ በባለራዕዮቹ፡ በሀገራዊ መልዕክታቸው የሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ልብናቀልብ የገዙት፡ በሚሊዮን ወጣቶች ብረት ዘብ የቆሙት፡ አሽከርነትን የሚጠየፉ፡ ሎሌነት ያልፈጠረባቸው፡ ሰው መሆን ክቡር ነው የሚል መርህ ከነፍሳቸው ጋር የተጋመደባቸው መሪዎች እጅ የሚገኘው አዲሱ ኦህዴድ እንጂ።

የለማ- አብይ ኦህዴድ ለትግራይ መሪዎች ያልተጠበቀ ዱብእዳ ሆነባቸው። እንደፈረስ ሊጋልቡት የሚችሉት አይደለም። ከዕውቀት ነጻ በሆነ አእምሮ ጠፍጥፈው የሰሩት፡ ምርኮኞችን ሰብስበው እስትንፍስ ዘርተው ያቆሙት ኦህዴድ እነለማ እጅ ሲገባ እንደኤርታሌ ፍም እሳት የማይጨበጥ የማይነካ ሆነባቸው። ትላንት ዛሬ አይደለም። ጊዜ ተቀይሯል። ዘመን ተለውጧል። የትግራይ ገዢ ቡድን ትዕቢት ተንፍሷል። ኦህዴድ እግር አውጥቷል። ጥርስ አብቅሏል። እጁን ይዘው መንገድ የሚመሩት፡ እንደአሻንጉሊት የሚጫወቱበት ዘመን አልፏል።

ምንግዜም የበላይ ሆኖ መቀጠል አለበለዚያም ሞት የሆነባቸው እነስብሃት ነጋ የመጣባቸውን አደጋ የሚሻገሩበት አንዳች ተአምር ማግኘት አለባቸው። በስብሰባ ሞከሩት። አልሆነም። ግምገማ ተቀመጡበት። የሚቻል አይደለም። በደህንነት፡ በጸጥታ ሃይሎች ወከባና ማስፈራራት ሁኔታውን አዩት። አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ....ሲሆንባቸው ተዉት። የቀራቸው አንድ ዕድል ብቻ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ። በዚህ ኦህዴድ ማንበርከክ ካልቻሉ የአጼ ዮሀንስን ዘውድ ለመቶ ዓመታት የማንገስ ህልማቸው አፈር ከድሜ በልቶ እነሱም ከነቅሌት ታሪካቸው መወገዳቸው አይቀርም። እናም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሞት ሽረት ጉዳይ ነበር። ህልውናቸውን የሚያስቀጥል የመጨረሻ ዕድል ነው።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግልጽ ኦህዴድ ላይ የተሰነዘረ ሰይፍ ነው። መከላከያ ሰራዊት ያለእኛ ፍቃድ በክልለችን ምግባት አይችልም የሚል ኮስተር ያለ አቋም የያዙትን እነለማን በአስቸኳይ አዋጅ ስም ለማንበርከክ የትግራይ ገዢ ቡድን አሰፍስፏል። ወገኖቻችን ላይ አንተኩስም የሚል አቋም የያዙትን የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶችን ትጥቅ ለማስፈታት ቋምጧል። የገበሬውን መሬት አትፈነጩበትም የሚል ጠንከር ያለ ውሳኔ ያስተላለፈውን ኦህዴድን መልሶ በቁጥጥር ስር ለማድረግ እነስብሃት ቸኩለዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስት የተለጠጠ ስልጣን ተሰጥቶት እንዲዋቀር የተፈለገውም ለዚሁ ነው። ከጸጥታና ሰላም ባሽገር የመሬት ጉዳይንም እንዲመራ አድርገው ያዋቀሩት ያለምክንያት አይደለም። የኦህዴድን አመራርና የጸጥታ ሃይል በአስቸኳይ አዋጁ በመጠርነፍ፡ አፉ ተሎጉሞ፡ እጅና እግሩ ተቀፍድዶ፡ በሂደትም ተዳክሞ ኮስምኖ እንዲቀር፡ በመጨረሻም የተነቃነቀውን ዙፋን በማረጋጋት በአዲስ ጉልበት ረግጦ ለመግዛት እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም።

አስቸኳይ አዋጁ በፓርላማው ህግና አሰራር ውድቅ ሆኗል። ድምጽ ለማግኘት በየሀገራቱ የተላኩትን አምባሳደሮች ሳይቀር ያስመጡት፡ ተሰባስበው ገብተው አዋጁን ለማጸደቅ ይሉኝታ ባጣ መልኩ የተረባረቡት የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት ቁጥር አልሞላ ሲላቸው እንደፈረስ በሚጋልቡት ታማኝ አገልጋያቸው አባዱላ አማካኘነት ሰርዘውና ደልዘው በጉልበት ጸድቋል ያሉበትና ዓለም የታዘባቸው ሂደት የሚያሳየው አስቸኳይ አዋጁ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ነው። አቶ አባዱላና ጥቂት የኦህዴድ ሰዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የታወጀውን ሞት እጅና እግራቸውን አውጥተው መደገፋቸው በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ የሚቀመጥ አሳፋሪ ተግባር ነው።

ሆነም ቀረም፡ ተደልዞና ተሰርዞ የጸደቀው አዋጅ ኦሮሚያ ክልል ላይ አነጣጥሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። እንድተባለውም ኦህዴድን የማዳከም ስራ በስፋት እየተካሄደ ነው። እነለማ መግለጫ እንዳይሰጡ በአዋጁ ተቀፍድደው ተይዘዋል። ኮማንድ ፖስቱ የኦሮሚያን ፖሊሶች ትጥቅ ካላስፈታሁ አስቸኳይ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ አልችልም የሚል ሪፖርት አቅርቧል። ከወዲሁ አምስት የኦህዴድ ባለስልጣናት በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ውለዋል። የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲራዘም ተደርጓል። የትግራዩ ገዢ ቡድን አባዱላ በሚባል አገልጋዩና በሌሎች የኦሮሞን ህዝብ አሳልፈው ለአራጅ በሰጡ የኦህዴድ አባላት እየታገዝ የእነለማን ኦህዴድ በማጥቃት ላይ ተጠምዷል። ምንም እንኳን የህዝብ ድጋፍ በአስተማማኝ ደረጃ ከጀርባ ያላቸው እነለማ ለጊዜው በጀመሩት ፍጥነት መጓዝ ባይችሉም በዚህን ቀውጢ ጊዜ የህዝባቸውን አደራ የሚዘነጉት አልሆነም። እንደሰማሁት ኦህዴድ ኢህአዴግ ከሚባለው የህወሀት ዣንጥላ ለመውጣት እየመከረ ነው። መውጣቱ ብዙ ፖለቲካዊ ዋጋ ቢያስከፍለውም እንደአንድ አማራጭ በመፈተሽ ላይ ነው።

የትግራዩ ገዢ ቡድን በጭፍን እየሮጠ ነው። የስልጣን ስግብግብነት ልቦናውን ደፍኖት በጥፋት ጎዳና ላይ እየሸመጠጠ ነው። ኦህዴድን ለማዳከም የጀመረውን እንቅስቃሴ በሚቀጥሉት ሳምንታት በስፋት እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል። እንግዲህ የህዝብ ጉልበት የሚፈተሸውም እዚህ ላይ ነው። የትግራዩን ገዢ ቡድን ከመሬት ቀብሮ፡ ከነጉድፉ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ መዝግቦ ለሁሉም የሆነችዋን ኢትዮጵያን በነጻነት ደሴት ላይ ለማስቀመጥ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ አንድ መሆን ያለበት ጊዜ ላይ ነን። እነለማን ሊሰለቅጥ ጥርሱን እያፏጨ ያለውን የትግራይ ገዢ ቡድን ጥርሱን አወላልቆ ከታሪክ ገጽ ላይ የማጥፋት ሃላፊነቱን ከዳር ማድረስ ምርጫ የሌለው እርምጃ ነው። ለጥገናዊ ለውጥ እየተሯሯጠ ያለውን አገዛዝ እስከወዲያኛው የማሰናበቱን የተጀመረ ስራ መጨረስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
መሳይ መኮንን

Monday, March 5, 2018

የሕዝቡን ትግል እናግዝ !

የፈረንሳዩ አለም አቀፍ የዜና አውታር የሆነው ራዲዮ FRI። 06:37 ሰዓት ላይ የኢ/ያ ዋና ከተማ አ.አበባ ዛሬ በመንግስት ላይ በተደረገው አድማ ሳቢያ የንግድ ስራዎች በብዙ ቦታዎች ተዘግተውና ሲስተጓጎሉ ውለዋል ብሎናል።በቀጣይ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል እንከታተል።የአቅማችንም እናድርግ።
ጎበዝ እየተሰራ ያለውን ምእራባውያኑም አውቀውታል።ችግሩ እኛ የምናይበት አተያይና የለመድነው ለዘመናት የተከተልነው የትጥቅ ትግል ስልት ካልሆነ ብለን ሙጥኝ ማለታችን ሲሆን ይህንን እስከመጨረሻው ድረስ ላናየው እንችላለን። ሊቢያን የመንን ሱዳንን ኢራቅን ሶርያን ምን እንዳደረገ እያየ ዘላቂና አዋጭ የተባለውን የትግል ስልት ነው ሕዝብ እየተከተለ ያለው።እድሜ ለተማረ!!! በመንደርና በደደቢት ልጆች ጭንቅላት የሚያስቡ ሰዎች የሚመራ ትግል አይደለም።
ነጮቹንም ግራ ያጋባቸው ቀድሞውን የሚያውቁት በአፍሪካና በአረብ አገራት የሚያዩትና የሚያውቁት የጦር መሳሪያ ትግልን ማየት አለመቻላቸው የበለጠ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ የከበዳቸው በመሆኑ እንደቀድሞው እያለሳለሱ መቀጠላቸውን አቁመው ጠንከር ቆንጠጥ የሚያደርግ መግለጫ እያወጡ የቀድሞው አጋራቸው የነበረው ሊባል እንደደረሰ ተረድተው አሰላለፋቸውን ከህዝብ ጎን ማድረግን የመረጡ ይመስላሉ።
ስለዚህ በያለንበት እንደየአቅማችንና በተናበበ መልኩ እየተግባባን የሕዝቡን ትግል እናግዝ።የራሳችንን እየተውንና እያጣጣልን የነጀዋር የነእንትና እያልን ከንቱ መመኘት እናቁም። አሁን ወያኔ ጉሮሮው ተይዞ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ላይ ነው ያለው።ነፍስ እንዳይዘራ ባለው ላይ ማጥበቅ ነው የሚበጀን።

የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሜ/ ጀነራል ገብሬ ዲላ ከሃላፊነቱ መነሳቱ ታወቀ!!

ESAT
የጸጥታኃይሎች እናማህበረሰብ

የጸጥታ ኃይሎች ዜና (የካቲት 25, 2010 ዓ.ም)

------------------------------------
ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያን ለ10 ተከታታይ አመታት ያክል በሃላፊነት ተመድቦ ዋና መምሪያውን እንደ ፈለገ ሲፈልጥና ሲቆርጥ የነበረው ሜ/ ጀነራል ገብሬ ዲላ በህይወትና በሃገር ሃብት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱ ይታወቃል። በተለይ በ1999 ዓ.ም በሱማሊያ እስላሚክ ኮርትን ለመውጋት በሚል ሰበብ ባልተጣና እና በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዞ 43ኛ ክ/ጦርን እየመራ እንዲገባ በማድረግ ሰራዊቱ እንደቅጠል እንዲረግፍ አድርጓል። ክፍለ ጦሩም እንዲደመሰስ በማድረግ ሰራዊቱን በትኖ በመሸሽ የራሱን ህይወት ብቻ ያተረፈ እንደሆነ ይታወቃል። ሜ/ ጀነራል ገብሬ ዲላ ለፈጸመው ክህደት እና ከፍተኛ ጥፋት ተጠያቂ ከሚሆኑት የህወሃት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል አንዱ መሆን ሲገባው እሱ ግን ስልጣንን በላይ በላዩ በመደራረብ የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ እስከመሆን የደረሰ ነው።
ጀነራል ገብሬ ዲላ ምንም አይነት ለቦታው የሚመጥን ብቃት ሳይኖረው ወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያን ለ10 ተከታታይ አመታት እንዲመራ የተደረገው ከመከላከያ ኤታ ማዦር ሹም ከጀነራል ሳሞራ የኑስ ጋር በነበረው ቅርብ ወዳጅነት መሆኑን ይነገራል። ስለሆነም በ2000 ዓ.ም ጀነራሉ ወደ ወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊነት የመጣው ከጀነራል ሳሞራ የኑስ ጋር የነበረውን ቅርብ ግንኙነት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ አካላት ይገልጻሉ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ተከትሎ የሳሞራ ስልጣን ከቀን ወደ ቀን እየተሸረሸረ የሚገኝ ሲሆን፣ ለሳሞራ ስልጣን መሸርሸር እንደዋነኛ ምክንያት የተቀመጠው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃልፊ ጌታቸው አሰፋ እንደሆነ ከመከላከያና ከደህንነቱ በየጊዜው አፈትልከው የሚወጡ መረጃዎች በመጠቆም ላይ ናቸው። አቶ ጌታቸው አሰፋ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የሳሞራ የኑስን ስልጣን አስለቅቆ በምትኩ የራሱን ቅርብ ሰዎች በሳሞራ ወንበር ለመተካት ያስችለው ዘንድ የሳሞራን ተከታዮች አስቀድሞ መምታት የሚል ስልት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት እየገለጹ ይገኛሉ።
በዚህም መሰረት በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጀነራል ገብሬ ዲላ ከወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊነቱ ተነስቶ በምትኩ ለሌላኛው የህወሃት አባል የሆነው ሜ/ ጀነራል አታክልቲ በርሄ ቦታውን እንዲወስድ ተደርጓል። ሜ/ ጀነራል አታክልቲ በርሄ አሁን የወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሆኖ ከመሾሙ በፊት በመከላከያ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ደህንነት ውስጥ በሃላፊነት ሲሰራ የነበረ ነው። የአሁኑ ተሿሚ ሜጀር ሜ/ ጀነራል አታክልቲ በርሄ ልክ እንደ ገብሬ ዲላ ሁሉ ለቦታው የሚመጥን ምንም አይት መሰረታዊ እውቀት እንደሌለው ጀነራሉን በቅርበት የሚያውቁት በመከላከያ ውስጥ የሚገኙ አካላት ይገልጻሉ። ሜ/ ጀነራል አታክልቲ በርሄ በዘረፋ ከፍተኛ ሃብት ያካበተና በሙስና የተጨማለቀ እንደሆነ ይታወቃል። በእርግጥ በህወሃት ቤት ታማኝነትና አገልጋይነት እንጂ ሙያዊ ብቃትና ልምድ ለሹመትና ሽልማት እንደማያበቃ በ27 ዓመታት የህወሃት ታሪክ መመልከት ተችሏል።

Wednesday, January 31, 2018

ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ

ታላቅ ሃገራዊ ውይይትና የመዝናኛ ምሽት በኦስሎ ኖርዌይ Sathurday Feb.3,2018 ከ14 ሰአት ጀምሮ!

ኢትዮጵያውያን ህብረታችን ውበታችን መገናኘታችን ደግሞ የጥንካሬያችን ምንጭ ነውና ኑ ሰብሰብ ብለን ስለሃገራችን እየመከርን ዘና እንበል፣፣

03.02.2018 ከ14: 00 ጀምሮ  በባህላዊ ምግብና መስተንግዶ የታጀብ የመመካከሪያ ልዮ ስብሳባ  ስለተዘጋጀ በኖርዌይ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተጋብዛችዋል !!!

በዚህ ስብሰባ በሃገራችን ጉዳይ ላይ የተለያዩ ድርጅቶች  እና ግለሰቦች ከሚያራምዱት የልዩነት ሃሳብ ባሻገር በጋራ አንድ ሊያረጉን በሚችሉ ሃሳቦች ላይ እንወያያለን፣ እዚሁ ኖርዌይ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በጋራ እንዴት  መቁዋቁዋም እንደሚቻል እንማከራለን ::

በዚሁ ዝግጅት በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች በደብዳቤ  የተጋበዝሁ በመሆኑ በዝተን የምንታይበት እና የበዛ ሃሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ ይሆናል::

እርሶም ከወዲሁ  ቀኖኑን  ከኛ ጋር ለማሳለፍ ያቅዱ !!!
ስብሰባችንን ታላቁ አርቲስት ሻንበል በላይነህ በባህላዊና ሐገራዊ ዘፈን ያደምቀዋል !!!

ቦታ : አንቲሬሲስት ሴንተር የስብሰባ አዳራሽ :: ( Storgata 25 , 0184 Oslo )

የስብሰባው አስተባባሪ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጭ ድርጅት በኖርዌይ ::