Monday, April 14, 2014

አንድ ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ነው? ወይስ ሲፈቀድለት? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11818/

April 14, 2014
በአለፈው ሳምንት (ፋክት ቁጥር 36) ወይዘሮ መስከረም የተለያዩ መጻሕፍትን በመጥቀስ በሴቶች ላይ ያለውን መጥፎ ጫና በደንብ ያስመሰከረች ይመስለኛል፤ ግን እኮ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የቆየ፣ ክፉና ጎጂ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፤ ቁም-ነገሩ ያለው ከዚያ የባህል ጭነት በራስ ጥረት ወጥቶ፣ ነቀፌታንም ሆነ እርማትን ለመቀበል ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንደመስከረም በአደባባይ ሀሳብን በመግለጽ በአገርና በወገን ጉዳይ መሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ የተቻለን ሁሉ ማድረጉ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ይህንን መልስ የምጽፈው፤ ወይዘሮ መስከረም በአጋጠሟትና በምታያቸው እንቅፋቶች ላይ ማተኮርዋ እንደርስዋ መንፈሳዊ ወኔው የሌላቸውን ያስፈራራቸዋል እንጂ አያበረታታቸውም፤ የማንንም አፍአዊ ጫና ተቋቁመው በራሳቸው የውስጥ ኃይል እንዲመሩ እናድርግ።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
አንድ መጽሐፍን በመጥቀስ ወይዘሮ መስከረም የሚከተለውን ጽፋለች፡–
ፈጣሪ የሠራውን ውጫዊ ገጽታን ማሽሞንሞን በቂ እንደሆነ ሲነገራት የኖረች ሴት፣ በምን ተነሳሺነት አእምሮዋን የሚመግብ እውቀት ልትሻ ትችላለች? … በልጅነት እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት በጉብዝና ወራት አላዋቂ በመሆን ቢወቀስ ትርጉም አይኖረውም፤ …››
ወይዘሮ መስከረም ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው (ልብ በሉ ሴት አላልሁም፤) መሆንዋን እንዴት እስከዛሬ ሳታውቅ ቀረች? ባለመጽሐፉም ይሁን መስከረም የሔዋንን ታሪክ ሳያነሡ መቅረታቸው መሠረታዊ ስሕተት ነው፤ በተጠቀሱት ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አንድም እውነትን የሚመስል ነገር የለም፤ መስከረም‹‹የሔዋን ዘር›› ከማለት በፊት የሔዋንን ሥራ ቆም ብላ ብታስታውስ የጠቀሰችውን መጽሐፍ እኔ እንደምነቅፈው ትነቅፈው ነበር፤ የሔዋን ታሪክ የሚነግረን የሚከተለውን ነው፡ ‹‹ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤›› ዘፍ. 3
የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ማለት ‹‹እንደእግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ›› ሆኑ ማለት ነው፤ አሁንም ሔዋን መስከረምና ባለመጽሐፉ እንዳቀለሏት አለመሆንዋን መረዳት ይቻል ነበር፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል! በአንጻሩ አዳም የፍርሃት አባት ነው፤ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤›› ያለው እሱ ነው! ስለዚህ ወይዘሮ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› የምትለውን በድላለችና ይቅርታ መጠየቅ ሳያስፈልጋት አይቀርም!
ሔዋን የተጠቀመችው ውጫዊ ገጽታን የሚያሽሞነሙን ሳይሆን የውስጥን የመንፈስ ኃይል ቆፍሮ በማውጣት ነበር፤ በዚህ የውስጥ ኃይል ለሚጠቀም ከውጭ ግፊት አይጠብቅም።
‹‹እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት›› አይወቀስም፤ ትላለች ወይዘሮ መስከረም፤ እየተገፉ የሚገኘው ባርነት ነው፤ እውቀት የሚገኘው በነጻነት ነው፤ መገፋት ከእውቀት ያርቃል እንጂ ወደእውቀት አያስቀርብም፤ የመስከረም ዋናው መልእክት ሰላቢውን እንጂ ሰለባውን አትውቀስ የሚል ነው፣ ወይም የኔ ሀሳብ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ዓይነት ሆኖባታል፤ ለመሆኑ ሰለባ የሚሆን ከሌለ ሰላቢ ይኖራል ወይ? ሰለባ ከመሆን በፊት ሰለባ ላለመሆን መጣር አንዱ የኑሮ ዓላማ አይሆንም ወይ? ከዚህ በፊት ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ደጋግሜ ጽፌ ነበር፤ ጭቆና የጨቋኙ ባሕርይ የሚሆነውን ያህል የተጨቋኙም ባሕርይ ይሆናል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የሚጠቅመውን ያህል ለተጨቋኙም ጭቆና ይጠቅመዋል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የኑሮው መሠረት የሆነውን ያህል ለሚርመሰመሱት የጨቋኝ ሎሌዎች ጭቆና የኑሮ መሠረታቸው ነው፤ እንዲህ እያለ ወርዶ ወርዶ የጭቆና ጠቃሚነት ለሎሌው ሎሌ፣ ለሎሌው ሎሌ ሎሌ … በኢትዮጵያ ምናልባትም የመጨረሻዋ የጭቆና ሰለባ ሚስት ትሆናለች፤ ወይም ልጆች ይሆናሉ! ጨቋኝና ተጨቋኝ የባሕርይ ቁርኝት አላቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ ወይዘሮ መስከረም ይህ እውነት ያልሆነበት ሁኔታ ወይም አጋጣሚ የምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤›› የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱትንና በቁማቸው የሞቱትን ሲያመሳስላቸው ነው! ለእኔ የሚታየኝ እንዲህ ነው።
መስከረም ብዙ ታላላቅ ሴቶችን ጠቅሳለች፤ በእስዋ ግምት ሁሉም በአባታቸው ወይም በባላቸው እየተገፉ ወደትልቅነት መድረኩ የወጡ ናቸው፤ አዙራ ብታየው የጠቀሰቻቸውን ሴቶች ገፉ የምትላቸው ወንዶች መጀመሪያውኑ በሴቶቹ ተገፍተው እንደነበረስ ሊታሰብ አይገባም? ምናልባት ከጠቀሰቻቸው ሴቶች ይልቅ መስከረም የሄለን ኬለርን ታሪክ ብታስታውስ ኖሮ መገፋትን አታነሣም ነበር፤ ሄለን ኬለር በሕጻንነትዋ ዓይኖችዋም ጆሮዎችዋም ሥራቸውን አቆሙ፤ የሄለን ኬለር የመንፈስ ጥንካሬ ከውስጥዋ አዲስና የተሻሉ ዓይኖችንና ጆሮዎችን እንድታበቅልና እንድትማር፣ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያዋ ሴት ምሩቅ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል፤ ይህች አስደናቂ ሴት ከመቶ ሠላሳ ዓመታት ግድም በፊት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የነበረውን አጥር ሰብራ፣ ዓይኖችዋ ባለማየታቸውና ጆሮዎችዋ ባለመስማታቸው የገጠማትን እክል አሸንፋ ራስዋን ከወንዶች በላይ ለማድረግ በቅታለች።
መገፋትን የሚፈልግ ሁሉ፣ ካልገፉት የማይነቃነቅ ሁሉ፣ ሬትን ሲግቱት ይጣፍጣል እያለ የተቀበለ ሁሉ፣ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ፣ እያሉ አታልለው እንኳን ዶሮ የለም ሹሮ ሲሉት የማይናደድ ሁሉ፣ ምኞቱ ልደግ ልመንደግ እያለ ሲነዘንዘው በአፈና ጭጭ የሚል ሁሉ ለወቀሳ ብቻ አይደለም ለውርደትም ክፍት ነው፤ ስለዚህም ተወቅሶ ከውርደት ከዳነ ወቀሳው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፤ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጆች ሁሉ — ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ-አሮጊት፣ ባለሥልጣን ተራ፣ ገበሬ ነጋዴ፣ ወታደር ፖሊስ፣ አስተማሪ አስተዳዳሪ፣ ዳኛ ጠበቃ፣ ሀኪም መሀንዲስ፣ … — የፈለገውን ቢሆን ላለበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የራሱና የግሉ ነው፤ ራሱን የሚገነባው ወይም ራሱን የሚንደው ራሱ ነው፤ ሰበብ እየፈለጉ ከዚህ ኃላፊነት መውጣት ቀላል ቢመስልም ተመልሶ እምቦጭ ነው፤ ዳገቱን ለመውጣት የሚመረውን እውነት መቀበል ያሻል።
በመጨረሻም በማናቸውም መንገድ፣ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ወደቁልቁለት የሚገፉትን ወይም የሚነዱትን ‹‹እምቢ!›› ብሎ ድምጹን ያላሰማ ገደል ገብቶ ሲንፈራፈር ከራሱ በቀር የሚወቅሰው የለም፤ አቅመ-ቢስነት ከውጭ አይመጣም።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ በኖርዌይ ኦስሎ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄደ April 14, 2014

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11826/

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ
Ginbot7 meeting in Norway
በዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ  የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አዘጋጅነት አፕሪል ቅዳሜ 12/2014  በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ  የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና የዲያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ተካሄደ:: በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከኦስሎ እና ከተለያየ ከተማ በመምጣት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን  የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ በመሆን ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል::
ሕዝባዊ ስብሠባው በኖሬጅያውያን የሰአተ አቆጣጠር ከቀኑ 15:00 እስከ ምሽቱ 21:00 ሰዓት የተካሄደ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አቢ አማረ በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አረመናዊ ስርአት በጭካኔ በግፍ ለተገደሉ እና በተለያዩ አስር ቤቶች በፖለቲካ ኣስተሳስባችው ምክንያት ያለወንጀላች የሚስቃዩ ውድ ኢትዮጵያዊን ወገኖቻችን በማስብ  በዚሁ ዘረኛ ቡድን አስቃቂ የኣካል ጉዳት ለተፈጸባቸው ኢትዮጵያዊን  የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማስደረግ ስብሰባውን አስጀምረውታል::
በመቀጠለም አቶ ዮሀንስ አለሙ የዴምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር የመግቢያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ስለ ዲምክራሲያዌ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አመሰራረት እና ስለ ድጋፍ ድርጅቱ አላማ በማብራራት የድጋፍ ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት በሀገር ቤት በሰላማዊ ትግል የወያኔን መንግስት ለመጣል እየታገሉ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶችን እየረዳ እንደሚገኝ እና ከሀገር ውጭ ደግሞ የወያኔን መንግስት  በሁለገብ ትግል  ለማስወገድ እየሰራ ያለውን የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅትን በግንባር ቀደምነት እየረዳ እንዳለ በመግለጽ  የወያኔን ዘረኛ ስርአት ለመጣል ሁሉም ሰው አስተዋጿ ማድረግ እንደሚጠበቅበት እና ማንኛውም  ኢትዮጵያዌ ዜጋ በሀገራችን የጋራ ጉዳይ ስለሆነው  የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሀሳብ በመለዋወጥ ፣በመካከላችን ያሉትን ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ኋላ በመጣል ፣ በመቻቻል፣ ሀገር እያፈረሰ እና ሕዝብ እያዋረደ ያለውን የዘረኛውን የወያኔን መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁለገብ ትግል ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበት አጽኖት ሰጥተው ንግግር አድርገዋል::
Ethiopians public meeting in Norway
በመቀጠለም ዲምክራሲያዊ ለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል የሆኑት አቶ ቡዙነህ ፅጌ የስብሰባው ተጋባዥ እንግዳ ሰፊውን ጊዜ በመውሰድ ከንጉሱ ስርአት ጀምሮ በደርግ መንግስት ዘመንም በሀገራችን የተደረጉ የፖለቲካ ንቅናቄዎችንና ለውጦችን አንድ በአንድ በመዘርዘር አሁን ካለው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ጋር በማነጻጸር ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ላይ ሀገሪቱን እየመራው ነው የሚለው የወያኔ መንግስት ከዚህ ቀድሞ ኢትዮጵያን ከመሩት ከሁለቱ መንግስታቶች ማለትም ከንጉሱም ከደርግም መንግስት ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ እንደማይገናኝ የወያኔ መንግስት ዘረኛና የዘረኝነት ፖለቲካ እያራመደ ያለ አረመናዊ መንግስት እንደሆነ አብራርተዋል::
የግንቦት 7  የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ቡዙነህ ፅጌ አክለውም ከወያኔ በፊት የነበሩ ሁለቱ መንግስታቶች ለውድቀት የዳረጓቸውን ምክንያቶች በመጥቀስ የወያኔን አንባ ገነናዊ መንግስት ለአፋጣኝ ውድቀት ሊዳርጉት ይችላሉ የሚሉትን ግልጽ ምክንያቶች በመዘርዘር አስቀምጠዋል:: አቶ ቡዙነህ በሁለት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማንሳት እና በማብራራ ከሕዝብ ውይይት እንዲያደርጉበት ለመወያያ ያቀረቡ ሲሆን እነዚህም:
1, በሙስሊሙ ማህበረሰብ እና በወያኔ መካከል ያለው ግጭት
2, የህዳሴ ግድብን  በማስመልከት ያለው ተቃውሞ
ስለሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ሲናገሩ የሙስሊሙ ትግል በሁለት አመታት ውስጥ የተደረገው ሰላማዊ ትግል በጣም የተሳካና ወያኔ በቀላሉ ሊያዳፍነው ያልቻለው ሰላማዊ መብትን የመጠየቅ ትግል እንደሚያደንቁ በመናገር ነገር ይህ በሙስሊም ማህበረሰብ በኩል እየተደረገ ያለው ትግል እስከ አሁን ድረስ ከመንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ሊያገኝ እንዳልቻለ እና ወደፊትም ከወያኔ መንግስት በኩል ምንም አይነት መልስ ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል:: ለዚህም ማስረጃው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከጠየቋቸው አራት የመብት ጥያቄዎች አንዱም ካለመመለሱ በተጨማሪ እስካሁን መሪዎቻቸውም በሃሰት ውንጀላ በእስር እየማቀቁ ያለፍርድ እየተንገላቱ መሆናቸው ነው::
ነገር ገን አሁን እየሆነው ባለው ሁኔታ በእንደዚህ አይነት መንገድ እስከመቼ ድረስ የሙስሌሙ ትግል ይቀጥላል በማለት የተናገሩ ሲሆን አሁን እየሄደ ባለው አካሄድ የሙስሊሙ ተቃውሞ የትግል አቅጣጫውን እስካልቀየረ ድረስ ረጅም ርቀትን ትግሉ ሊቀጥል ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ነግር ግን የሙስሊሙ ጥያቄ ከእምነት መብት ጥያቄ ባሻገር ወደ የዜግነትን መብት ወደ ማስከበር መለወጥና መሸጋገር  እናደለበት በመናገር የሙስሊሙ ማእበረሰብ ጥያቄ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው  ትግሉ በዚህ መልኩ ሲቀጥል እንደሆነ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰተዋል::
በሁለተኛም የህዳሴ ግድብ በሚመለከት  ያቀረቡት ሀሳብ ወያኔ የራሱን የፖለቲካ ኪሳራና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ በዕድገት ስም ለመሸፈን ያመጣዉ እንጂ ታቅዶበትና ለህዝቡ በማሰብ እንዳልሆነ በኢትዮጵያና በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉ ግፍ እንደ ማስረጃነት በማቅረብ ያብራሩ ሲሆን እንደ ምሳሌም ወያኔ ሃገራዊ የሆነ አላማ ይዞ ካለመነሳቱ አንፃር የሃገርን ድንበር አሳልፎ እስከመስጠት እየሄደ ያለበትን ሁኔታ ጠቅሰው ይህ አሰራር ደግሞ የዲክታተሮች ባህሪ እንደሆነ አብራርተዋል::
የወያኔ መንግስት በህዳሴ ግድብ ሰበብ ምክንያት በማድረግ በመላው አለም ኢትዮጵያኖች በሚኖሩበት ሀገሮች በመዞር የዲያስፖራውን ቀልብ ለመውሰድ የሚያደርገው የአባይ ቦንድ ሽያጭ ሩጫ በዲያስፖራ ተቃዋሚዎች አማካኝነት በፍጹም እንዳልተሳካለት ይህንንም የወያኔ በአባይ ቦንድ ሽያጭ ስም ገንዘብ ዘረፋ በመቃወም ወያኔን አሳፍረው ከመለሱት መካከል በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እንደሆኑ በማስታወስ  የዚህ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰበብ የወያኔን መንግስት ወደ መጥፎ ውድቀት ላይ ሊጥለው እንደሚችል በማመን የወያኔ መንግስት በአሁን ሰአት ከግብጽ መንግስት ጋር እየገባ ያለው ሰጣ ገባ ለኢትዮጵያ መጥፎ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ንግግራቸውን አጠቃለዋል::
በመቀጠልም አቶ ብዙነህ ባነሷቸው ነጥቦችና እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰፋ ያለ ውይይትም ተደርጓል፥፥ ከውይይቱም በማስቀጠል የዲምክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንሄል አበበ የዲምክራሲያዌ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የአቋም መግለጫ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ድርጅታቸው ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ፈጽመው እንደሚያወግዙ እና ዴምክራሲያዌ ለለውጥ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሁል ጊዜ ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዲሞክራሴ ንቅናቄ ጎን እንደሚቆም ቃል በመግባት የአቶ ቡዙነህ ፅጌን በኖርዌይ በመገኛት ለህዝቡ ለሰጡት ገለጻ አመስግነዋል::
በዝግጅቱ መጀመሪያና ማጠቃለያ ላይ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል መዝሙር በመዘምራን የተዘመረ ሲሆን በየጣልቃው የተለያዩ የባህል ዘፈኖች በተወዛዋዦች ታጅቦ የቀረበ ሲሆን ጣእም ያለው ባህላዊ ምግብም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የሴቶች ክፍል ተስተናግዷል፥፥ ስብሰባውን ተጀምሮ እስኪያልቅ አቶ ፍቅሬ አሰፋ መርተውታል::
በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ለዝግጅቱ መሳካት የበኩላችሁን ላበረከታችሁና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች ረዥም ርቀት በመጓዝ የዝግጅቱ ታዳሚ ለነበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን እና እንዲሁም የድርጅቱ አባላቶች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ

በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብ በመቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ April 14, 2014

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11830/

Ethiopians demonstration in Norway
በ11-4-2014 በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን የወያኔን የስለላ መረብና ኖርዌ በስደተኛው ላይ ያላትን ፖሊሲ በመቃወም    የተቃውሞ ሰልፍ አረጉ።  23 ዓመት እራሱ መራጭ እራሱ ተመራጭ ሆኖ በጠመንጃ አፈሙዝ ህዝቡን እያንቀጠቀጠ የኖረው ወያኔ አንድ ቀን ሕዝብ በቃኝ ብሎ አንቅሮ እንደሚተፋውና ንብ ሆኖ ለነፃነቱ እንደሚነሳ ማወቅ ነበረበት።
ግን አልሆነም ዜጎች እንደዜጋ በሐገራቸው መኖር ቀርቶ በስደትም ሰላማቸውን ማግኘት አልቻሉም።
እስርና እንግልት፣ረሐብና ሰቆቃ፣ስደት የእያንዳንዱ እጣ ፋንታ ሆነ፤በወያኔ ዘመን ሰው ብቻ አይደለም መሬትም መሰደድ ጀምሮ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል የኢትዮዽያን ለም መሬት ለሱዳን በመሸጥ ላይ ይገኛል
ኢትዮዽያንና ኢትዽያዊነትን ያሉ ሁሉ አሸባሪ እየተባሉ በየእስርቤቱ ታጉረው እጣ ፈንታቸው እስርና እንግልት ሆነ ሐገራቸውን ጥለው በባሕርና በየብስ አቆራርጠው የሞተው ሞቶ የተረፈው በአለም ዙሪያ ተበትኖ ጥገኝነት  በመጠየቅ ይኖራል::
በዚሕም የተሳካላቸው ጥቂቶች ሲሆኑ ባብዛኛው ወያኔ ለውጩ አለማት በሚያሳየው ሁለተኛው ፊቱ ምክንያትና ምእራባውያን ከሐገሪቱ ከሚያገኙት ጥቅም የተነሳ ሐገርህ ዲምክራሲ ነው እየተባለ ፍትሀዊ ያልሆነ መልስ እየተሰጠው በመጉላላት ላይ ይገኛል።
ያም ሆኖ የሐገሩ ጉዳይ በደም ስሩ ሰርጎ የገባው ኢትዮዽያዊ ሁሉ ጠዋት ማታ ኢትዮዽያዬ እያለ ይጮሀል። ይህ የህዝብ ቁጣ ያስፈራው ወያኔ ያለ የሌለ የሐገሪቱን ኢኮኖሚ እየመዘበረ ዜጎችን ይሰልላል ያሰልላል፣አልፎ ተርፎም ዜጎችን ከመሰሎቹ ጎረቤት ሐገሮች ድረስ በመሄድ ጎትተው እስርቤት ያስገባሉ።
ይህንን ለመቃወምና ለማውገዝ ነበር የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ኢትዮዽያውይኑ ዛሬም ስለ ሐገራቸው ሊጮሁ የወጡት፤ ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን እንዲህ በማለት ነበር ድምፃቸውን ያሰሙት እኛ ስደተኞች እንጅ ወንጀለኛ አይደለንም፣ኖርዌ ለማፊያው ወያኔ የምታደርጊውን እርዳታ አቁመሽ ከኢትዮዽያ ሕዝብ ጋር ቁሚ፣ወያኔ የሚያደርገውን ተግባር እናወግዛለን፣ሼም ኦን ዩ ሳውዝ ሱዳን ኦኬሎን አሳልፈሽ የሰጠሽ፣ወያኔ አሸባሪ ነው፣ለውጥ እንፈልጋለን፣ኖርዌ የዩኤንን ህግ ታክብር የሚሉትን የመሳሰሉ ሲሆን
በሰልፉ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኢትዮዽያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ተወካይ አቶ ዳንኤል የወያኔን ጀሌዎች የማጋለጡ ስራ በሚገባ እየተሰራበት መሆኑን ሲገልጡ ሰልፈኛው በጭብጨባ የተቀበላቸው ሲሆን የስደተኛ ማህበሩም ተወካይ ኖርዌ ነፃ እንድታወጣን ሳይሆን ለወያኔ የምትሰጠውን እርዳታ አቁማ ድጋፍ እንድትሰጠን ነው፤ በተጨማሪም ኖርዌ አቶ ኦኬሎን ታስለቅቅ በማለት  ተጠይቃለች። በሰልፉ ላይ የኖርዌ ሊብራል ፓርቲ ተወካይ ከሰልፈኛው ደብዳቤ ተቀብለው መልክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን የኖዋስ ፣አንቲረሲስት ተወካዮችም እንዲሁ ይዘውት የመጡትን መልክት ለሰልፈኛው አስተላልፈዋል።
ከዚያ በቀጥታ ወደሶፊን በርግ ሎካል አዳራሽ ሰልፈኛው አምርቶ ምሳ  ከተበላ በሁዋላ ኮሚቴው ካባላቱ ጋር ሰፊ ዉይይት ያደረገ ሲሆን የ፫ወር የስራ ሪፖርትም አቅርቦአል።
የኢትዮዽያ ስደትኞች ማህበር በኖርዌ

Friday, March 28, 2014

ያልታሰረው ማን ነው??

ሰሞኑን አንድ ኢትዮጵያዊ በቶሮንቶ የህሊና እስረኞችን ለመዘከር በግሉ አዳራሽ ተከራይቶ
የአንዱዓለም አራጌን “ያልተሄደበት መንገድ” የሚለውን መጽሃፍ ለሽያጭ በአቀረበበት ቦታ ተገኝቼ ነበር።
በዚህ አዳራሽ አንዱዓለምን፣ እስክንድርን፣ ርዕዮትን …ወዘተ ለመዘክር ብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ብዛት
ስመለከት “በእውነቱ እስረኞች እኛ ነን ወይስ እነ ዓንዱአለም?” የሚል ጥያቄ ጫረብኝ። አገርን ያህል
ትልቅ ነገር ከራሳችን የፖለቲካና የግል ጠባብ ፍላጎት ዙርያ ቀንበበን ልንከተው ስንቸገርና አልሆንልን ሲል
ደግሞ እርስ በርሳችን ስንጎነታተል አሁን አለንበት የመከራ ዘመን እንድንቆይ በራሳችን የፈረድን መሆኑ
ግልጽ ይሆናል።
ትንሹን ህይወታቸውንና ጠባቡን የግል ፍላጎታቸውን በትልቁ ለሚያይዋት ኢትዮጵያ የሰውትን
ወንድሞቻችንን ልናስታውስ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ብዙዎቻችን በተረባረብንና የነሱን ከባድ
መስዋዕት በትንሽ በትንሹ በተጋራናቸው ነበር። እውነቱ ግን ያ አይደለም። ለብዙዎች የእንቅስቃሴያችን
ማዕከል ሁሉ “እኔ” ስለሆነ ከዚያ የተለየን ማውገዝ፣ ማደናቀፍ፣ አለመተባበር…ተግባራችን የሆነ
ይመስላል።
አንዱዓለም እንዳለው ከዚህ በፊት ያልተሄደበትን የመቻቻልና የመከባበር መንገድ መጀመር
የጊዜው ጠቃሚ እርምጃ ነው። ይህ ሁኔታ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ የዮሃንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቁጥር3 እስከ 11
“ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘች ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርስዋን አቁመው
መምህር ሆይ ይች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴ እንደነዚህ ያሉትን እንዲወገሩ በህግ አዘዘን።
አንተስ ስለእሷ ምን ትላለህ? አሉት።….ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በደንጋይ ይውገራት
አላቸው።…እነሱ ይህንን ሲሰሙ ህሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ
አንድ እያሉ ወጡ” ይላል። ከኛም መካከል ህሊናው የሚወቅሰው ካለ ከተሳሳተ ድርጊቱ መቆጠብ አለበት።
በዚሁ መጽሃፍ ቅዱስ የሉቃስ ወንጌል ላይም “በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፤ በራስህ
ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ለምን አትመለከትም?” ሲል ይደግመዋል። እያንዳንዳችን የምንከተለው መንገድ
ትክክል ሊመስለን ይችላል። የሌሎችን ሆነ የእኛን ትክክለኝነት የሚዳኘው ተግባራችንና ጊዜ ነው።
እስከዚያው ግን መከባበርና መተባበርን የመሰለ ትልቅ ነገር የለም።
ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሰዎች ሆነ ተራው ግለሰብ የራሳቸውን ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ስህተት
ላይ ብቻ ማተኮር ሲጀምሩ የውድቀታቸው መነሻ ይሆናል። ማንም ሰው ሲሠራ ሊሳሳት ይችላል።
መጥፎው ነገር ከስህተት አለመማር ነው። ስህተቱን በጸጋ የሚቀበልና የሚያርም ትልቅ ነው። በእስልምና
እምነትም ሃዲስ ላይ (በትክክል መጥቀስ ባልችል ይቅርታ ይደረግልኝ) እንዲህ ይላል “የማያውቅ ሆኖ
የማያውቅ መሆኑን ማወቅ የማይፈልግ ቂል ስለሆነ ሽሸው። የማያውቅ ሆኖ አለማወቁን የሚያውቅ ከሆነ
ልጅ ነውና አስተምረው። የሚያውቅ ሆኖ አዋቂ መሆኑን የማያውቅ ከሆነ ቀስቅሰው፤ ተኝቷልና። አዋቂ
ሆኖ አዋቂነቱን የሚያውቅ ከሆነ ጥበበኛ ነውና ተከተለው” የብዙዎቻችን ባህሪ ባንዱ ሁሉ የሚካተት
ነውና ቦታችንን ማወቅና እርምጃችንን ማስተካከል የተገባ ነው። ስለሆነም የታሰሩ ወንድምና እህቶቻችን
የተሸከሙት እዳ ከግላችንና ከቡድናችን ፍላጎት በላይ አገራዊ ስለሆነ ከመጎነታተል፣ ከመከፋፈል ወጥተን
አገራዊ ስፋት ባለው አላማ ዙርያ በጋራ መቆም ይኖርብናል። ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስና “ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት” የሚለው ለትናንቶቹና
ለዛሬዎቹ ጠባቦች መንደርደርያ ማዕከላዊ ሃሳብ ቢሆንም ደጋግመው እንደሚናገሩት ይህንን ብሂል በሃቅ
ለብሄር ብሄረሰብ ነፃነት አልተጠቀሙበትም። ያ ቢሆን ምንኛ በታደልን። ድርጊታቸው ግን ተቃራኒ
በመሆኑ ኢትዮጵያን ወደ ገሃነምነት ቀይረዋታል።
 በአምደጽዮን፣ በፋሲለደስ፣ በቴዎድሮስ፣ በዮሃንስ፣በምኒልክ፣ በሃይለስላሴ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ
ማበብ ነበረበት ብሎ የሚያስብ አእምሮ ቅንነት አለው ብለን አንጠብቅም። እነዚህ ነገስታት ግዛታቸውን
ለማስፋት፣ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ባደረጉት እንቅስቃሴ ጭካኔ የተሞላበትን መንገድ መሄዳቸው
ግልጽ ነው። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እናስተዳድራለን ብለውም አያውቁምና የሚጠብቅም አልነበረም።
ዳኝነታቸው ርህራሄና ፈሪሃ እግዜብሄር ያለበት እንዲሆን ሁሌ ባያከብሩትም ይናገራሉ፤ ህዝቡም
ይጠብቃል።
ዛሬ በትናንት ታሪክ ታስረን፣ ለዚያ የከፋ ድርጊት ከመካከላችን ተጠያቂ ፍለጋ ስንኳትንና አጽም
ለማውጣት መቃብር ስንቆፍር የሁላችን መቀበርያ አዳዲስ መቃብር እየተዘጋጀልን መሆኑን ዘንግተናል።
በተለይም በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የገዙን ሁለቱ ስርዓቶች ማለትም ደርግና ወያኔ ካለፉት ነገሥታት
በባሰና በዘገነነ ሁኔታ ጨካኞች ናቸው። አገሪቱንም ወደ ሙሉ እስር ቤትነት የቀየሯት እነዚህ አምባገነኖች
ያለፉትን አገዛዞች በኮነኑበት አንደበት የራሳቸውን ትልቅነት ከመስበክ ወደ ኋላ አላሉም። በነዚህ አገዛዞች
“ኢትዮጵያ የዜጎች ሁሉ እስር ቤት ናት” የሚለው ከፀሃይ የደመቀ ዕውነት ነው።
ይህን ዓለም ያወቀውን እውነት በመካድ የትናንቶቹ አምባገነኖች መንግስቱ ኃይለማርያምና
ፍቅረስላሴ ወግደረስ የነሱ አገዛዝ ፍትህ የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲ የሞላበት የሚያስመስል ስንክሳራቸውን
አሳትመው እንደጲላጦስ እጃቸውን ሊታጠቡ ይዳዳቸዋል። ፍቅረስላሴ “እኛና አብዮቱ”ባለው መጽሃፉ
ቢያንስ ለታሪክና ለህዝብ ክብር ትንሽ የቅንንነት ጥፍጣፊ እንኳ ጨምሮበት ‘ሰርተን ያለፍነው ስህተት ይህ
ነበር፣መጪው ትውልድ ከእኛ ስህተት ተምሮ መልካም አገር መገንባት አለበት’ የሚል እውነት በመጠኑም
ይዞ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ ለብቻቸው ያዝዟቸው በነበሩት ሠርቶ አደር ጋዜጣ፣አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ፣
ሄራልድ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ ሲያደነቁሩን የኖሩትን ፕሮፓጋንዳ ሃያ ሶስት ዓመታት ሲያመነዥከው
ቆይቶ ለህትመት ሲያበቃ የህዝቡንም የማስታወስ ችሎታ መናቁን አሳይቷል። ፍቅረስላሴ በእስር ባሳለፈው
ሃያ ዓመታት ወደ ኋላ በትዝታ መለስ ብሎ የሄዱበትን መንገድ ሁሉ በመቃኘት ወደ እውነቱ ቀርቦ መገኘት
ሲገባው ሲታሰር ተኝቶ ሲፈታ የነቃ ይመስል። የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድሞ ያለፈበትን የመከራ ዘመን ሆነ
አሁን እየደረሰ ያለበትን ጭቆና ዳግም እንዳይመለሱ በመታገል ላይ እያለ ፍቅረስላሴ ባንኖ በመንቃት ድሮ
የጻፈውም ሜሟር እንዳለ ይዘምርልናል። “በማይጨው ጊዜ የደነቆረ ስለማይጨው ሲተርክ ይኖራል”
እንዲሉ ስልጣን ሲለቁ እንደደነቆረና ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ በምን አስተሳሰብ ላይ እንዳለ
ለመገንዘብ ያልታደለ መሆኑ እንድናውቅ ያደርጋል።
ፍቅረስላሴ አሁን ድረስ የሚያመልክበትና በፍርሃት የሚያሸረግድለት መንግስቱ ኃይለማርያም
ብቸኛ አላማው የሆነውን የስልጣን ጥማቱን ለማርካት የህዝቡን ለጋ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በእድሜና
በልምድ መከበር የሚኖርባቸውን አዛውንት ኢትዮጵያውያንን፣ ጓደኞቹን ሳይቀር ተራ በተራ ሲያርዳቸው
ቆሞ ሲንቀጠቀጥ፣ ማረጃ ሰይፍ ሲያቀብል እንዳልነበረ የነሱን የፍጅት ዘመን ከወያኔ ጋር እያነጻጸርን
እንድንናፍቀው በተዘዋዋሪ ሊነግረን ይሞክራል። የኢትዮጵያን ጠላቶች በየፈፋው ያርበደበዱት እነጄኔራል ታሪኩ ላይኔ፣አማን አንዶም፣ አምሃ
ደስታ፣ ፋንታ በላይ ….ወዘት ዛሬ ተርፈው የተንሸዋረረ ታሪክ ሊነግሩ እንዳሉት በፍርሃት አልራዱም።
አምባገነኑን አምባገነን ነህ እያሉ ነው የሞቱት። ታሪካቸውን ራሳቸው ባይናገሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ
ያውቀዋል። ሲያከብራቸውም ይኖራል። እነሱንና አገሪቱ የገደሉት የታሪክ ዝቃጮች ስለሥራቸው ምን
ቀለም ቢቀባቡ ማንነታቸውን ሊደብቁ አይችሉም።
ለመሆኑ የአስራ ሰባት ዓመቱ የ“እኛና አብዮቱ” ውጤት ምን እንዳስገኘ ፍቅረስላሴ ይዘረዝረዋል?
ህዝቡንና አገሪቱን ቀፍዶ አስሮ ለወያኔና ለሻዕብያ ያስረከበው ማን ነው? “ወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንድያ
የሚመርጥ” ብሎ መንግስቱ ሃይለማርያም የሰደበውን ህዝብ አንተም በተጠያቂነት ታቀርበው ይሆን?
አዎ ኢህአፓዎች፣ መኢሶኖች፣ወዝሊጎች፣ ማልሬዶች፣ ሻዕብያዎች፣ ወያኔዎች፣ ኦነጎች…..በዚች አገር
ውድቀት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ለማወቅ ህዝቡ የፍቅረስላሴንና የጓደኞቹን
ምስክርነት የሚፈልግ አይደለም። ምንም እንኳ ይህ ነበር የኛ ድርሻ ለማለት ድፍረቱን ባያገኙትም ህዝብና
ታሪክ የሁሉንም አስተዋፆ አይረሳውም።
ቀበሌዎችን፣ የጦር ካምፖችን፣ መኖርያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ሁሉ ወደ እስር ቤትነት
የቀየረ፣ ወላጆች የልጆቻቸውን አስከሬን ለመቀበል የተገደሉበትን ጥይት ዋጋ ያስከፈለ፣ አልቅሰው እርም
እንዳያወጡ የከለከለ፣ አዛውንቱን ኃይለስላሴን ያለፍርድ ገድሎ መቃብራቸው ላይ መፀዳጃ ቤት
የሰራ…ወዘተ ይህን ሁሉ ያደረገ የደርግ ስርዓትና መሪዎቹ የሌሎችን ያነሰ ስህተት የሃጢያታቸው
መጠራረጊያ ፎጣ ሊያደርጓቸው የሚያስችል የሞራል ብቃት የላቸውም።
የመሬት አዋጅን እንደትልቅ ድል ደጋግሞ ማንሳቱም የሚገርም ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን
የተዋደቁለ የመሬት ጥያቄ በደርግ ሆነ በወያኔ አልተመለሰም። አዋጁ መሬትን ከመሬት ከበርቴዎች ነጥቆ
ገበሬውንና መሬቱን የአምባገነኖች ንብረት ነው ያደረገው። ወያኔዎችም ካባታቸው ደርግ ደህና አድርገው
ተምረዋልና ኢትዮጵያዊ የመሬት ባለቤት የሚሆነው “በኢህአዴግ ሬሳ ላይ ነው” ሲል መለስ ዜናዊ
ደምድሞታል።
ከገበሬው የወጣን ነን የሚሉት የደርግ አባላት ሆኑ ለገበሬው ቆሜያለሁ የሚሉት ወያኔዎች
በካድሬዎቻቸው አማካይነት ንብረቱና ራሱን ገበሬውን የራሳቸው የግል እቃ፣ በቤቱም ውስጥ እስረኛ
አድርገውታል። በህብረት እንዲያርስ የተገደደውና በችጋር የተጠበሰው የአርሲ ገበሬ “በናንተ ህብረት እርሻ
ያተረፍነው በርሃብና በተባይ ማለቅን ነው” ብለው ብልቃት ሙሉ ቅማል ለደርግ ባለስልጣን
ማሳየታቸውን በወቅቱ በቦታው የነበርነው ጋዜጠኞች ተመልክተናል። ይህን እውነት በአብዛኛው አገሪቱ
ለሥራ በተዘዋወርሁባቸው ወቅት ባይኔ አይቻለሁ።
ደርግ የጀመረውን የአፈና መንገድ ወያኔዎች በረቀቀና በሰላ መልኩ ተጠቅመውበታል። የመሰረት
ደንጋዩን ያስቀመጡላቸው ግን እነፍቅረስላሴ ናቸው። ወያኔ አገርን በመበተን ከደርግ የከፋ ቢሆንም
የደርግን ዘመን የሚናፍቁ ካሉ የዚያ ስርዓት ተዋናዮችና ተጠቃሚዎች የነበሩ ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ
ህዝብ ከሁለቱም አምባገነኖች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይገባዋል።
ወደ ተነሳሁበት የእስር ጉዳይ ልመለስና በደርግ ሆነ በወያኔ መታሰርን በተደጋጋሚ ቀምሼዋለሁ።
ለምን ታሰርሁ ብዬ አልቆጭም። ከህዝቡ መከራ የተጋራሁበት እውነተኛ የህይወቴ ምዕራፍ ስለነበር ባሰብሁት ቁጥር መጠነኛ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል። ሁለቱም ስርዓቶች በጣም ፈሪዎች ስለሆኑ በጣም
ጨካኞች ናቸው። የተማሩትንና ለስልጣን ተቀናቃኝ ይሆናሉ ያሉትን ማሰርና በግፍ መግደላቸው እንዳለ
ሆኖ በሁለቱም ስርዓቶች የሰባና የሰማንያ ዓመት በጤና የደከሙ ከፊሎችም ዐይናቸው የታወሩ
አዛውንቶች ያለፍርድ እስር ቤት ቀስ እያሉ በሞት ሲያሸልቡ አይቻለሁ። መደገፍያ ከዘራቸውን ማንሳት
የማይችሉትን አዛውንትና ክፉና ደግ የማያውቁ ህፃናትን የስርዓታቸው ተቀናቃኝ አድርገው የሚባንኑ
አምባገነኖች ናቸው ሁለቱም።
ያ ሁሉ መጨፍጨፍ፣ ያ ሁሉ እስር የደርግን ስርዓት ከመፈራረስ፣ መንግስቱን ከመፈርጠጥ፣
ጓደኞቹን እነፍቅረስላሴንና ለገሰን እንደበግ ከመጎተት አላዳናቸውም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወያኔዎች
ግድያውን፣ እስሩን ካስተማራቸው ከደርግ በባሰ ሰልጥነው ውድቀቱንም እየወረሱት ነው። የተፈጥሮአቸው
እድገት ጣርያ (ክላይማክስ)ላይ ደርሰው ቁልቁለቱን ጀምረዋል። የገነቡት ሁሉ እየተናደ እንዳይቀብራቸው
ራስን የማዳን ጥድፊያ ላይ ተጠምደዋል። ይህ መንፈራገጥ ግን የበለጠ ሚዛናቸውን እያሳታቸው ቁልቁል
ይወረውራቸዋል። ሲወድቁ በሚያደርጉት መንፈራገጥ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸው ግን የተጠበቀ ነው።
የወያኔ የአጥቂነት ጊዜ አልፎበት አሁን በመከላከል ላይ ተጠምዷል። ጅኒው ከጠርሙሱ ወጥቷልና መልሶ
የመክተት አስማት የሚሠራ አልሆነም።
 ታላቁ ሩስያዊ ደራሲ፣ የታሪክ ምሁርና የሶብየትን አምባገነንነት አጥብቆ ይተች የነበረው
አሌክሳንደር ኢሳየቪች ሶልዝሄንጺን የሩሲያውያንን መከራ ለዓለም በሚገባ ካሳወቀባቸው በርካታ
ሥራዎቹ ዘ ጉላግ አርፒላጎ የዘረዘራቸውን ስናነብ ደርግና ወያኔዎች ያንን እያነበቡ የፈጸሙ ይመስለናል።
በአንደኛው ጽሁፉ “እኛ በሚሊዪን የንምቆጠር ሩስያውያን ሴቶችና ወንዶች ከቀን ቀን፣ ከዓመት ዓመት
ራሳችንን ደፍተን ወደ እስር የምንጎተትበት ምክንያት ይህ ነው። የማስጠንቀቂያ ደወል አናጮህም።
በጎዳናዎች ተቃውሟችንን አናሰማም። እንዲያውም በተቃራኒው በጎዳና ላይ በጓደኞቻችን ፊት ስንነዳ እኛ
ግዞተኞች ምንም እንዳልተፈጸመብን ፊታችንን ቅጭም አድርገን አንገታችንን ደፍተን፤ እነሱ የነገ
ግዞተኞችም እኛን እንዳያዩ ዐይናቸውን መሬት ላይ ተክለው እንተላለፋለን። ህዝባችን ይህንን ድርጊት
ሂደቱን ሳያዛባ ተግባራዊ ማድረጉን ተክኖበታል። በብዙ ማሰቃየት የታጀበው ምርመራ ሲጠናቀቅ እኛ
ትንንሾቹ አሳዎች መረባቸው ውስጥ ዋኝተን እንገባላቸዋለን። …ባህሩን የሞላን ጥሩ አሳዎች፤
የአጥማጆቻችንን መንጠቆ ጉሮሮአችን ውስጥ ለማስገባት የምንሽቀዳደም፤ እኛን በመጎተት እንዳይደክሙ
ወደ ላይ ቀዝፈን የምንቀርብላቸው…..” እያለ ለአምባገነኖች የመከራ ማገዶነት ምንም ሳይንፈራገጡ ወደ
ማረጃው፣ ወደ እስሩ የሚሽቀዳደሙ ሩሲያውያንን የሸነቆጠበት አነጋገር እኔንም እንዳለንጋ መንፈሴን
ይተለትለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በመደበኛ እስር ቤቶች፣ በጦር ካምፖችና በድብቅ እስር ቤቶች የሚማቅቀውን
ኢትዮጵያዊ ቁጥር ማወቅ ይከብዳል። በደፈናው እኛና ዓለም የሚያውቃቸው ደፋርና ለዴሞክራሲ ስርዓት
ማበብ ከፍተኛ መስዋዕት በመክፈል ላይ ያሉትን አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣
ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበከርና ጓደኞቹ ……እያልን ብንዘረዝር ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በአካል የተገደቡ እስረኞች ናቸው ብንልም በመንፈስ ልዕልና ያላቸው
ንፁሃን ናቸው። በእኔ አስተያየት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ቀሪው ኢትዮጵያውያን ነን እስረኞች እላለሁ።
እስክንድር፣ አቡበከር፣ ውብሸት፣ ርዕዮትና አንዱዓለም በአካል ከታሰሩበት ወህኒ ዘልቀው በመንፈስ ነጻ
መሆናቸውን አሳውቀውናል። ያሉበትን መከራ እንደ ኢምንት በመቁጠር የምንከፍለው ቀላል ነው እያሉ ምንም ለመክፈል ያልተዘጋጀነውን፣ ከዳር ቆመን በፍርሃት የምንርደውን ህሊናችን እንዲሞግተን በመተው
ባለ እዳ አድርገውናል።
ርዕዮት፡ “በኢትዮጵያ ፍትህ ማጣትና ጭቆና የተንሰራፋ በመሆኑ ለህይወቴ አዳጋ ይኑረውም
አይኑረው ለእውነት እቆማለሁ” ብላለች። ይብላኝ ለእኔና ለእናንተ ዳር ለቆምነው።
አንዱዓለም፡ “ያልተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ ከእስር ቤት ጠባብ ክፍል በጻፈው መጽሃፉ
“እስር የስቃይ ብቻ ቢሆንም ከነፃነትና ከዴሞክራሲ እጦት አይከብድምና በጸጋ መቀመል ነበረብኝ” ሲል
የአካል ስቃይን ፈርተን ህሊናችንን ለአሰርነው አማራጩን ይነግረናል። ከዚያም አልፎ “ይህ ሁሉ የመከራ
ሸክም የማን ነው? የታሳሪ ፖለቲከኞች ብቻ ወይስ የነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉ?” በማለት የፍትህና
የነፃነት ናፍቆታችን አፋዊ በመሆኑ ህሊናችን እንዲወቅሰን ጥያቄውን ወረወረልን።
እስክንድር፡ ሰሞኑል ለልጁ (ርዕሱ ለልጁ ይሁን እንጂ መልዕክቱ ለእኛ ነው) ከእስር ቤት በፃፈው
ደብዳቤ “በጣም ናፍቄሃለሁ። እናትህንም ጭምር። ስቃዩ አካላዊ ስቃይ ብቻ ነው የሚሆነው።
የቤተሰባችን ስቃይ ለረጂም ጊዜ መከራ ከተሸከመው ህዝባችን ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው።ከዚህ የበለጠ
ክብርም የለም።ስቃዩን ሁሉ በመቋቋም፣ የሚቻለውን ሁሉ ርቀት በመሄድ፣ማንኛውንም አቀበት
በመውጣት፣የትኛውንም ባህር በማቋረጥ ነፃነት ላይ በመድረስ ጉዞአችንን ማጠናቀቅ አለብን። ከዚህ ያነሰ
ትግል ህሊናን ማደህየት (ባዶ ማስቀረት)ነው” ሲል ጽናቱንና የምንሄድበትን እርቀት አመልክቶን
“አምባገነንነት ፍርሃት የነገሠበት በመሆኑ መንግስታዊ ሽብር፣ እስራትና ማሰቃየት ዋነኛ ተግባሩ ነው።
በዚህ መንገድ ግን ሁሉንም ህዝብ ማንበርከክ አይቻልም። ነገር ግን የተወሰኑ ሰዎችን የጥቃት ኢላማ
በማድረግ ብዙውን ሰው በፍርሃት ማደንዘዝ ይችላሉ። በጥቁር ዓለም ጥንታዊ የመሆናችን የጋራ ኩራት
ይህንን አስማት ለመጨረሻ ጊዜ እንድንሰብረው ያስገድደናል” ሲል በነሱ መታሰርና መሰቃየት ሩቅ ሆነን
በፍርሃት ተሸብበን የታሰርነውን ሊፈታን ይታገላል።
ሌሎችም እስረኞች ደጋግመው በተለያዬ መልክ ያስተላለፉልን መልዕክት ይሄው ነው። ኢትዮጵያ
ውስጥ ያለው ህዝብ በአጠቃላይ እስረኛ መሆኑ ቢታወቅም ውጭ ያለነው እንኳ በፍርሃት፣ በራስ
ወዳድነት፣ በክፍፍል፣ በመከነና የትም ባላደረሰን የትናንት አስተሳሰብና ከዚያም አልፎ በስሜታዊነት
እስረኛ ነን። አንዱዓለም፣ እስክንድርና ሌሎችም የሚሉን ‘አሳሪ ሳይኖራችሁ ራሳችሁን ያሰራችሁ ራሳችሁን
ነፃ አውጡና ትልቅ አገራዊ ዓላማ ይዘን አገር ነፃ እናውጣ’ ነው የሚሉን።
የጽሁፌ ማጠቃለያው ሁላችንም እስረኞች ነን።በመጀመርያ ራሳችንን ነፃ እናውጣ። ከዚያ የታሰሩ
ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንንና አገራችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን።
ግለሰብ ሆኖ በህሊናው፣ ድርጅት ሆኖ በአሰራሩ ነፃነት ከሌለው ለነፃነት ቆሜያለሁ ማለት
ከአፋዊነት አይዘልም። እስከ አሁንም የሆነውና ያየነው ይህንኑ ነው። ራሳችን ለራሳችን የነፈግነውን ነፃነት
ከአምባገነኖች በልመና አናገኝም።
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ!
ጸሃፊውን በamerid2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል
ethioforum.org  

Tuesday, March 25, 2014

መታመን በቀድሞ ነው !!

https://www.zehabesha.com/amharic/archives/13847
የሰሞኑ የኪዌት ጉዳይ ሁላችንንም እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው በተለይ በቅርቡ ከሳውዲ አረብያ የችግር ትኩሳት ትንሽ መብረድ ጋር ተያይዞ  በኪዌት የባለ ስልጣን ልጅ መገደል የወገኔን ችግር   ያብስዋል ብዬ  ነገሩን ትኩረት ሰጥቸው  እየተከታተልኩ ነው :: በጣም ትኩረቴን የሳበው እና የታዘብኩተ  የኪዌት የፓርላማ አባላት ተወያይተው የወሰኑት ጉዳይ ነው ::
The lawmaker stressed the need to oblige housemaids to undergo tests regularly to ensure they are not suffering from any psychological illness. 
.የቤት ውስጥ ሰራተኞች ቅጥር ውደ ኪዌት ሲመጡ የአምሮአቸው ሁኔታ ይጠና ማለታቸው ትክክል ቢሆንም እኔ ግን በትዝብት እና በግርምት ነው የተመለከትኩተ :: ምነው ስንቱን ወገኖቻችንን ሲገድሉ ሲያርዱ ሲያንገላቱ የነሱን የራሳቸውን  አእምሮ ሁኔታ አለማጤናቸው ?? እውነት ትክክል የሆነና ያልሆነ  ነገር ለካ እንደ ሃገሩ ይለያያል እነሱ ሲፈጽሙት እና እኛ ስንፈጽመው የሚሰጠን ስያሜ ለየቅል ነው ለካ :: በአረቡ አለም ስንት ህሊናን የሚያስትና እሚያንገፈገፍ ዘግናኝ ግፍ ተፈፅሞብን እንዳለፈ ቤቱ ይቁጠረው እውነቱን ነው ትልቁ መጽሓፍ ያለው " በራስክ ውስጥ ያለውን ትልቁን ምስሶ የሚአክል ጉድፍ እያለ የወንድምክን ትንሽዋን የአይን ጉድፍ ላውጣ ማለቱ ............" የሚለው  የሚስማማቸው ይመስለኛል::
            ያገራችን  መንገስትም ለአንድ ዜጋው የሚሰጠው  ክበር ሰለሌለ የሚከፍለው ዋጋ የዛኑ ያህል የከፋ ነው:: አንድ ዜጋ በሚፈጥረው ችግር ህብረተሰበን ብሎም አገርን እንደሚጎዳ በቅጡ የተገነዘበው አልመሰለኝም እኔ ሳስበው ችግሩ ሁላችንንም ያካትታል በተለይ መንግስትን!!! " ምቼም መንግስት የሚታመነው በባለፈው ስራው ነው" በተለይ አረብ አገር ባሉ ዜጎቻችን ላይ ሲበደሉ  ሲገደሉ መሬት ለመሬት ሲጎትቱአቸው አሁን ያለው መንግስት ለወገኑ ጥብቅና ሲቆም ሲታገልላቸው መብታቸውን ለማስከበር ደፋ ቀና ሲል አላየንም ከነሱ ጋረ ሆኖ በችግራችን ላይ ችግር ሲጨምርብን እንጂ !!  በየሃገሩ ተበትነው ያሉ ዜጎቻችን አለሁ የሚል  መንግስት ወገን ከሌለ ምኑን መንግስት ሆነልን!!  አገር ውሰጥም ተገብቶ ጭቆናወና ችግሩ እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ አሁንም እንዳየነው ፍልሰቱ መቀጠሉ የማይቀር ነው :: በቅርቡ ከሳውዲ የተመለሱት ወዳገራቸው ገብተው በያቅጣጫው ወደ ውጭ  የተበተኑት ይሄ ያደባባይ ሚስጥር ነው :: እና ለዚች ወገናችን  ከተብደለችው አንጻር ፍርድዋ እንዲቀልላት በጎ አደራጊ ደረጅቶች ወይ ገለሰብ እንድረስላት ::

 



 

Monday, March 17, 2014

“ኢህአዴጋዊ ምርጫ” በሰሜን ኮሪያ ኪም ጆንግ ኧን 100% ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል!

kim un
ድምጽ የመስጫው ጊዜ ተጠናቅቆ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ መቁጠር በጀመሩ ጊዜ ኪም ጆንግ ኧን የማሸነፋቸው ጉዳይ አሳስቧቸው በስጋት ውስጥ ነበሩ፡፡ ቆጠራው ተጠናቀቀ፤ ውጤቱ ይፋ ሆነ፤ አሸናፊው ታወጀ፤ ኪም ጆንግ ኧን ሥልጣን ከያዙ የመጀመሪያውን ምርጫ በ100% አሸነፉ፤ ከጭንቀታቸው አረፉ፤ ሕዝቡም በደስታ ፈነጠዘ፣ የክት ልብሱን ለበሰ፤ በአደባባይ ወጥቶም ዳንኪራ ረገጠ፡፡
korea2እሁድ በተደረገው ምርጫ የተሰጠውን እያንዳንዱን ድምጽ ኪም ጆንግ ያለተቀናቃኝ የራሳቸው አድርገዋል፡፡ በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው ምርጫ የተሳተፈው ሕዝብ የምክርቤት አባላትንም መርጦዋል፡፡ በደንቡ መሠረት ምርጫው የሚካሄደው ለምክርቤት ምርጫ ሲሆን የተመራጮች ዝርዝር ውጤት ከመታወቁ በፊት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት ኪም ጆንግ ኧን ያለተቀናቃኝ በተወዳደሩበት ወረዳ አንድም ተቃዋሚ ድምጽ ሳይሰጥባቸው የሁሉንም መራጭ ይሁንታ በማግኘት መመረጣቸውን ዘግቧል፡፡ ያለፈው ምክርቤት 687 መቀመጫ የነበሩት ሲሆን የአሁኑ ምን ያህል እንደሚኖረው እስካሁን አልታወቀም፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጠቃቸውና የኒዎሊበራል አቋም የሚያራምዱ ጽንፈኛ ኃይሎች ታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተከፈለበትን ምርጫ በማጣጣል ልማታዊውን መሪ መመረጥ ለመቃወም ቢሞክሩም “ምርጫው የኮሪያ ሕዝብ በታላቁ መሪ ኪም ጆንግ ኧን ላይ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳየበትና በእርሳቸው ራዕይ ለመመራት መወሰኑን በአንድ ድምጽ የገለጸበት ነው” በማለት የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት አጣጥሎታል፡፡
ምርጫ በተደረገበት እያንዳንዱ ወረዳ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የቀረበ ሲሆን መራጮች ድምጽ ሲሰጡ የሚመርጡት በተወዳዳሪው ስም አቅጣጫ “እመርጣለሁ” ወይም “አልመርጥም” የሚል ብቻ እንደነበር ተገልጾዋል፡፡ በህመምና በተለያዩ ምክንያቶች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው መምረጥ ለማይችሉ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ሳጥን ተዘጋጅቶ ያሉበት ቦታ የምርጫ ኮሮጆ በመውሰድ ድምጻቸውን እንዲሰጡ መንግሥት ያመቻቸላቸው መሆኑን የሰሜን ኮሪያ መንግሥታዊ ዜና አገልግሎት ጨምሮ ዘግቧል፡፡korea4
የሰሜን ኮሪያው ተሞክሮ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማድረግ ልምድ ላላቸው አገራት ተምሳሌት ከመሆኑ አኳያ በርካታ ልምምድ ሊወሰዱበት የሚችሉ እንደሆነ ምርጫውን የታዘቡ ገለልተኛ ያልሆኑ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በአንድ የምርጫ ቀበሌ አንድ ተመራጭ ብቻ “በማወዳደር” አላስፈላጊ የሆኑና የማያሸንፉ ተወዳዳሪዎችን በማስወገድና ወጪን በመቀነስ ልማታዊ ምርጫን ማበረታታት ከአሁኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ እነዚሁ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡
በምርጫው ወቅት አብዮታዊና አውራ ፓርቲያዊ ቀስቃሽ ዜማዎች የተሰሙ ሲሆን ሰሜን ኮሪያን ለ46ዓመት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጠ/ሚ/ርነት እና በፕሬዚዳንትነት አገልግለው የተሰውትን የቀድሞውን ባለራዕይ መሪ፣ የኮሪያ ላብአደር ፓርቲ ሊቀመንበር፣ የጦር ኃሎች አዛዥ፣ ማርሻል እና የሪፑብሊኩ ዘላለማዊ መሪ ኪም ኢል ሱንግን የሚያወሱ “በሌጋሲ” የተሞሉ ዜማዎችም ቀርበዋል፡፡
http://www.goolgule.com/eprdf-style-election-in-north-korea/ 

Wednesday, March 5, 2014

ኣፍሪካ ሃገራት የሚነሱ መሪዎች ስልጣን ላይ ከመጡ በሁዋላ ሁለት ነገር በጣም ይወዳሉ።


የሃገራቸው ነገር ሲነሳ የሚከነክናቸው ወገኖቻችን ኢትዮጵያ ላለባት ችግር መፍት ሄው ምንድነው?? እያሉ ኣጥብቀው ሲጠይቁ ይደመጣል። መፍትሄውም ብቻ ሳይሆን ችግሩ ማለትም እውነተኛው ችግር የት ላይ ነው ያለው??? ብለውም ኣጥብቀው ሲደመሙ ይታያል።
በርግጥም ሁላችን ኢትዮጵያዊያን የሆንን ችግሩ ምንድነው? ብለን ከጠየቅን ኣንዳንዶች ሊገረሙብን ይችላሉ። የችግሩ ተካፋይ ሆነን ሳለ፣ እየተጉላላን ያለነው እኛው ሆነን ሳለ፣ እንደገና መልሰን የሃገራችን ችግር የት ጋር ነው??? ብለን ስንጠይቅ የምናወጋቸው ሰዎች ምናልባትም ግራ ሊጋቡ ቢችሉ ኣይደንቅም። ነገር ግን መጠየቃችን ትክክል ነው።
በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ዳንዔል ላይ ኣንድ ናቡከደነጾር የተባለ ንጉስ ኣንድ ጊዜ ጠቢባንን ጠርቶ የህልም ፍቺ ይጠይቃል። ጥበበኞቹም ህልሙን ንገረንና ፍቺውን እንነግርሃለን ሲሉት ህልሙ ጠፍቶብኛል ስለዚህ ህልሙንም ፍቺውንም ውለዱ ብሎ ጉድ እንዳፈላ እናነባለን። እኛ ኢትዮጵያዊያን የዋናው ችግር ተጽእኖዎች የየእለት ኑሮኣችንን ሲያምሱት ብናይም ዋናውን የችግሩን ምንጭ መፈለጋችን ግን ኣሁንም ትክክል ነው።
የሃገራችንን ዋና ችግር የት ጋር ነው ብለን ኣጥብቀን ከጠየቅን በርግጥ የስርዓት ችግር ነው ወይ? ስርዓት በማጣታችን ነው ወይ የከፋ ችግር ላይ የወደቅነው? ብለን እንጠይቃለን። በዚህ ኣገባብ ስርዓት ስንል የኣይዲዮሎጂውን ጉዳይ ሳይሆን ፍትህና ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና የህዝብ የበላይነት የሚንሸራሸርበት ሲስተም ተዘርግቷል ወይ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው። ስለ ስርዓት ስናነሳ ደግሞ በዋናነት የሚታየው ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱ ነው። ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ምን ያህል ለዜጎች ይጨነቃል፣ ምን ያህል ለፍትህና ለነጻነት ለህዝቦች ጥቅም መንሸራሸሪያ ይህናል? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። በዚህ ረገድ በርግጥ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት ግን ችግራችን የስርዓት ችግር ሆኖ ኣናይም። ለኣብነት የ1955ቱን ህገ መንግስት ስናይ የፕሬስ ነጻነትን ይሰጣል፣ እኩል የህግ ከለላ ይሰጣል፣ የመሰብሰብ፣ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሁሉ ይሰጣል። የደርጉም ቢሆን ለዜጎች የሚጨነቅ ኣይነት ነው። “ኢትዮጵያዊያን በህግ ፊት እኩል ናቸው” ይላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የ1995ቱን ስናይ “ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው” ብሎ እጅግ ኣጠንክሮ ለዜጎች መብት መቆሙን ይደነግጋል። በውነቱ ይህ ኣንቀጽ ብቻውን ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ዋስትና ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ ተግባራዊው እውነት ደግሞ ለብቻው በተቃራኒው ተንሰራፍቶ ይታያል። ይህ ለምን ሆነ? እንዴት እንዲህ ሊሖን ይችላል? ብለን ነው መጠየቅ ያለብን። እንዲህ ስንጠይቅ የችግሩ ዋና ጉዳይም የስርዓት እጦት ሳይሆን ሌላ ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን። በርግጥ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ስርዓት ማምጣት ያስፈልጋል። በተለይም ብዙህነቱዋን ተንከባክቦ የሚይዝ ማህበራዊ የፖለቲካ ስርዓት ያሻናል። ያ ማለት ግን ከችግራችን እንድንወጣ ብቻውን ዋስትና ነው ማለት ኣይደለም። የቱንም ያህል ጥሩ ስርዓት ዘርግተን ከችግራችን ሳንወጣ ልንቆይ እንችላለን። ርግጥ ነው የማንነት ፖለቲካ ማህበራዊ ቀውስን ያመጣ ችግሮች የበለጠ እንዲነዱ የሚያደርግ ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ መንግስት ውድቀት በሁዋላ ከዚህ የፖለቲካ መዋቅር መውጣታችን ለመፍትሄ ትልቅ በር ኣለው። ይሁን እንጂ ኣሁንም ቢሆን የቱንም ያህል ቆንጆ ስርዓት እናምጣ ኢትዮጵያን ከመከራና ከርሃብ የሚያወጣት እሱ ብቻውን ኣይደለም። ታዲያ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መምጣት ኣለበት። ኣዎ፣ ዋናው የሃገራችን ችግር ያለው የፖለቲከኖች ስብእና ተክለሰውነት ወይም ፐርሰናሊቲ ጋር የተገናኘ ነው።
ሃገራችን ከችግር እንድትወጣ ከተፈለገ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። የችግሮቻችን ቁንጮም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እጦት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስንል ኣንድ ፓርቲ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የፍርድ ቤቱን ልጓም ለቀን መልሶ ከበላንም ይብላን፣ በራሳችን ላይ ይፍረድብን፣ ብሎ በራስ ላይ የመወሰን ኣቋም ነው። ወታደሩን ኣገርህን ጠብቅ የፓርቲ ጠባቂ ኣይደለህም ኣንተ ኣገር ጠባቂ ነህ ለማለት የፖለቲካ ሰዎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ፖሊሱን፣ ባንኩን፣ ሚዲያውን ሁሉ ልጓሙን ለቆ በሙያህ ኣገልግል ብሎ መወሰን ሲቻል ነው ከገባንበት ኣረንቋ የምንወጣው። የናፈቀንን ዴሞክራሲ በህይወት የምናየው። ጥያቄው ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዴት ሊመጣ ይችላል ነው። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ከራስ ጥቅምና ዝና በላይ የህብረተሰብን ዝናና ጥቅም በተጠሙ ሰዎች ሊነቃነቅ ይችላል። ኣንድ ቁርጠኛ መሪ ኣገር ሊለውጥ ይችላል። በታሪክ የታዩ ኣንዳንድ ቁርጠኛ መሪዎች በየሃገሩ ተነስተው ጥሩ መሰረት እየጣሉ ኣልፈዋል። በሃገራችንም የተጠማነው ይህንን ነው።
በኣሁኑ ጊዜ ተቃዋሚው ክፍል መንግስትን ኣጥብቆ ማውገዙ ትክክል ነው። የህዝቡም ልብ ነጸብራቅ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መንግስት በማንኛውም መንገድ ሲወድቅ ስልጣን ይዞ ጥሩ ስርዓት መዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነት (political commitment) ያላቸውን ሰዎች ይዘዋል ወይ? ብለን እንድናስብ ያደርገናል። በዚህ ረገድ ተቃዋሚው ጥቃቅን በሆኑ ፖሊሲዎች ከመከፋፈል ይልቅ ወደ ጋራ እያመሩ ከሁሉ በላይ የፖለቲከኞችን ስብእና የመገንባቱ ላይ ማተኮር ለነገይቱ ኢትዮጵያ ዋስትና ይሆናል። ይህን ስብእና ወይም ተክለሰውነት የመገንባት ስራ ፓርቲዎችን ቢዚ የሚያደርግ ወቅታዊ ስራ መሆን ኣለበት። ኢትዮጵያ በኣሁኑ ደረጃዋ ጥቃቅን ፖሊሲዎችን በማነጻጸር የምታማርጥበት ጊዜ ላይ ኣይደለችም። መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ያጣች በመሆኑዋ የስካንዲኒቪያው ኣይነት ዴሞክራሲ ይሻልሻል የኣሜሪካው ኣይነት? ማለቱ ያልበላትን የማከክ ያህል ነው። ሁሉቱም ሆኖላትስ ነው?
ዋናው በኣሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጉዳይ ፓርቲዎች እኔ እሻላለሁ ለማለት ዋናው መመዘኛቸው የተሰባሰቡት በተለይም ኣመራር ላይ ያሉት ግለሰቦች የፖለቲካ ቁጠኝነት ኣላቸው ወይ? ቁርጠኝነት በሞላቸው ሰዎች ቁጥር የትኛው ፓርቲ ያይላል? የሚል ልብ ያለው ድጋፍ ነው በተግባር የሚታየው ወይም መታየት ያለብት።
በቲየሪ ደረጃ በኣሁኑዋ ኢትዮጵያ በፍርድ ቤት ጉዳይ መንግስት ጣልቃ ኣይገባም። ይሁን እንጂ በተግባር ይገባል። ይገባል ብቻም
ሳይሆን ፍርድ ቤት የፖለቲካ መሳሪያ ነው። ኣሁን እዚህ ጋር የጎዳን የስርዓቱ ወይም የኣሰራሩ ጉዳይ ሳይሆን መከራ ውስጥ የከተተን ጉዳይ የግለሰቦች ስብእና ጉዳይ ሆኖ ነው የምናየው። ለምን እነዚህ ግለሰቦች ስርዓቱን ይጥሳሉ፣ ህጉ ለምን ኣቅም ያጣል? ካልን የፖለቲከኞቹ ላእላይ ስብስብ በተለያየ የግል ጥቅማጥቅም የተተበተበ በመሆኑ ነው። ድህነታችንም ኣንዱ ኣስተዋጾ ያደረገ ይመስላል። የተሻለ ስራ ለማግኝነት፣ ከድህነት ለመላቀቅ፣ ፖለቲካን መሳሪያ ማድረጉ የተለመደ መሆኑና ወደዚያ ጠጋ ያሉ ሃላፊዎች በዚህ ሞቲቭ የተሞሉ ስለበዙበት ስርዓቱ በቁሙ እንዲሞት ኣድርጎታል። በርግጥም በኣሁኑ የነጻነት ትግል ኣሰላለፍ በኩል ጎድሎ የታየው ይሄ ነውና ይህንን ማቋቋም ተገቢ ነው። ይህ ኮሚሽን ፓርቲዎችን እያበራታታ ይህን ተፈላጊ ስብእና በመገንባቱ ረገድ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ያደርጋል። ፓርቲዎችን በማቀራረብ ረገድ፣ የመፍትሄ ኣሳቦችን በማጠናቀር ረገድ፣ ለኣዲሲቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆነውን ኣዲስ ሰውነት በመጠቆሙ ረገድ ከባድ ሚና ሊጫወት ይችላል። ከዚያ በተረፈ ደግሞ እኛ ተራ ዜጎች መሪዎቻችንን የማጎልበትና ወደ ህብረት የመግፋት እንዲሁም ስብእናቸውን የመገንባት ሃላፊነት ኣለብን።
የብዙ ኣፍሪካ ሃገሮች ችግር ይሄ ይመስለኛል። ታግለን በብዙ መስዋእትነት ኣንድ ኣምባገነን ከጣልን በኋላ መልሰን በሌላ ኣምባ ገነን እንተካለን። ሌላው ኣለም እየተሻሻለ ሲሄድ ይሄኛው ክፍለ ኣለም ወደ ኋላ የቀረበት ትልቁ ምክንያት የነጻነት ታጋዮች ራሳቸው በሚገባ ለኣመራር የሚበቃ ስብእና ሳያዳብሩ ወደ ስልጣን ስለሚመጡ ነው።ደቡብ ሱዳን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። ለብዙ ኣመታት የነጻነት ትግል ታግለው፣ ብዙ ደም በመፍሰሱ ዓለም ሁሉ እነዚህ ሰዎች ቢገነጠሉ ይሻላል ብሎ ፈርዶላቸው ተገነጠሉ። የዳርፉሩን እልቂት የማያውቅ፣ ያልሰማ ያለም ክፍል የለም። ያ ሁሉ ሆኖ ኣዲስ ኣገር ከመሰረቱ በኋላ ገና ኣንድ ጊዜ እንኳን ምርጫ ሳያካሂዱ፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሳይመሰርቱ፣ ከሁለት ዓመት ያልዘለለ እድሜ ያላትን ኣገር በጎሳ ከፋፍለው ማመስ ጀመሩ።
ያለ መታደል ሆኖብን በኣንዳንድ ኣፍሪካ ሃገራት የሚነሱ መሪዎች ስልጣን ላይ ከመጡ በሁዋላ ሁለት ነገር በጣም ይወዳሉ። ኣንደኛው ዝና ሲሆን ሁለተኛው ገንዘብ ነው። ሁለቱም እጆቻቸው ይዘዋል። ባንዱ ስልጣን በሌላው ገንዘብ። ዝናውን ወደው ገንዘቡን ችላ የሚሉ ቢሆኑ ትንሽ ይሻል ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም በሃይል ስለሚወዱና ለዚህ የተሰጠ ስብእናቸው በውስጣቸው ስላልሞተ ክብ በሆነ ችግር ውስጥ እንድንወድቅ ኣድርጎናል።ኢትዮጵያዊያን በዚህ ላይ ልንነቃ ይገባናል። በተለይ የፖለቲካ ሰው መሆን የፈለጉ ወገኖቻችን፣ መሪ መሆን የሚሹ ወገኖቻችን በየጊዜው የባህርይ ለውጥ እያሳዩ በኣመለካከትና በሃላፊነት ስሜት እያደጉልን እንዲሄዱ እንሻለን። ከፍ ሲል እንዳልኩት እኛ ተራ ዜጎች ከውጭ ሆነን መፍረድ ብቻ ሳይሆን መሪዎቻችንን መንከባከብና ፍቅርን ክብርን ማሳየት ለፖለቲካ ቁርጠኝነታቸው ሃይል ይሰጣል።