Saturday, July 19, 2014

አንዋር መስጊድ እና አካባቢው ላይ ውጥረት ነግሷል


ከጁመአ ሰላት ጋር በተያያዘ የተቃውሞ መርሃ ግብር ነበር በስፍራው የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች እና መፈክሮች ነበሩ ::
ከነዚህ መካከል <<የታሰሩት ይፈቱ>> ፣ <<ድምፃችን ይሰማ >>፣ <<የሃይማኖት ነፃነትን ማክበር ግዴታ እንጂ መብት አይደለም >> የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችም ነበሩ ፡፡
የጁመአ ሰላት ሁለት ረከአ (ሁለት ጊዜ) የሚሰገድ ሰላት ነው ፡፡ ነገር ግን ብትላንትናው እለት ተሰግዶ ሳይገባደድ ማለትም አንደኛው ረከአ ላይ ብጥብጥ ሊፈጠር ችሏል፡፡
 ውጥረቱ ቀጥሏል በስፍራው ከነበሩ እማኞች መረዳት የሚቻለውም በተደጋጋሚ የቶክስ ድምፅ ተሰምቷል ፡፡
በወርሃ ረመዳን ላይ ይገኛል የሙስሊሙ ማህበረሰብ (በእስልምና እምነት ውስጥ ትልቁ የጾም ወር ነው) እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም የዛሬ ሁለት አመት 2004 ክረምት ላይ በዚሁ የፆም ወቅት ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሮ ነበር ፡፡
ባለፈው አመት ደግሞ በኢድ አልፈጥር በአል ቀን ከስግደት መልስ የተፈጠሩ ነገሮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
በትላንትናው እለትም ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አአባላት እና እንዲሁም ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርከት ያሉ የእምነቱ ተከታዮች የደረሰባቸውን ጉዳት በአካባቢው ወደሚገኙ መካከለኛ ክሊኒኮች እና ሆስፒታሎች እርዳታ እንደተደረገላቸው ነው።
 

Wednesday, July 16, 2014

ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የምርመራ መዝገቡ መዘጋቱ ሕገወጥ አካሄድ መሆኑ ተገለጸ

June16/2014


‹አሁን ታስረው የሚገኙበት ሁኔታ ሕገወጥና አደገኛ ነው›› የተጠርጣሪዎች ጠበቃ
zone 9999በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በክስ ላይ የሚገኙት ሦስት ጋዜጠኞችና ስድስት ጦማርያን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ፖሊስ ‹‹ምርመራዬን ስለጨረስኩ መዝገቡ ይዘጋልኝ›› በማለት መዝገቡ እንዲዘጋ ማድረጉ ሕጉን ያልተከተለና አደገኛ መሆኑን ጠበቃቸው አስታወቁ፡፡
ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሳዬና ጦማሪያንና የሕግ መምህር ዘለዓለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃኔ ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የሚቀርቡበት ዕለት ነበር፡፡ እንደወትሮው ሁሉ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ጓደኞቻቸውና የተለያዩ የችሎት ታዳሚዎች በጠዋት ማልደው በፍርድ ቤት ግቢ የተገኙ ቢሆንም፣ እስከ ቀኑ 5፡30 ሰዓት ድረስ ፖሊስም ሆነ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ችሎቱ አልመጡም፡፡ ከ5፡30 ሰዓት በኋላ ሌሎች ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎቹና ፖሊስ ችሎት ቆይተው ሲወጡ፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን፣ ደንበኞቻቸው ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቅረባቸውን ለማጣራት የዕለቱን ተረኛ ዳኛ ለማነጋገር ገቡ፡፡ ጠበቃው ስለደንበኞቻቸው ፍርድ ቤቱን ሲጠይቁ፣ ፖሊስ ምርመራውን መጨረሱን በማሳወቅ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዘጋቱን ሲያስረዳቸው፣ ‹‹እንዴትና በምን ሁኔታ?›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ከመዘጋቱ ውጪ ምንም ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
እስረኛ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የምርመራ መዝገቡ ሊዘጋ እንደማይችል የሚናገሩት ጠበቃ አመሐ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ መሆናቸው፣ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ምንም ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ በመሆኑ ድርጊቱ ሕገወጥና አደገኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ ምርመራውን ካጠናቀቀ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ይዞ በመቅረብ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳትና ክስ እስከሚመሠረትባቸው ድረስ በዋስ እንዲቆዩ ወይም የሕግ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት ስለሚቆዩበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠት እንደነበረበት አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ባልሰጠበት ሁኔታ ተጠርጣሪዎቹ ባሁኑ ወቅት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የሚናገሩት ጠበቃው፣ በወንጀል ሕጉና በሕገ መንግሥቱ በተጠሰው አካልን ነፃ የማውጣት መብት (ሐቢየስ ኮርፐስ) ክስ ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በሌላ የምርመራ መዝገብ የተካተቱት ጦማሪያን ማህሌት ፋንታሁን፣ አቤል ዋበላና በፈቃዱ ኃይሉ ደግሞ ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹም ሆኑ መርማሪ ፖሊስ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡
ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች ‹‹የመብት ተሟጋች ነን›› ከሚሉ የውጭ ኃይሎች ጋር በሙሉ ሐሳብና ገንዘብ በመስማማት ሕዝብን የማተራመስ፣ አገርንና መንግሥትን የማፍረስ ዘገባ በኢንተርኔትና በተለያዩ ድረ ገጾች ያልሆነ መረጃ ሲያስተላልፉ ተገኝተዋል በሚል ፖሊስ ሚያዝያ 17 እና 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለሁለት ጊዜ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ከተፈቀደለት በኋላ፣ በሦስተኛው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ውስብስብና ድርጊቱም የሽብርተኝነት ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀን እንዲፈቀድለት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ ተፈቅዶለት መመርመር ላይ መሆኑን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 78 ቀናት ሞልቷቸዋል፡፡
 
 

Monday, July 14, 2014

በኖርዌ የምንኖር ኢትዮጵያውያኖች በእልህና በቁጣ የተሞላ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረግን ።

ሰኞ ጁላይ 14, 2014 / ሓምሌ 7 ,2006

      የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ አዘጋጅነት በኖርዌ ኦስሎ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያኖች በአንድ ላይ በመሰብሰብ ከቀኑ 13፡00 ጀምሮ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ በየመን የፀጥታ ኃይሎች ታፍነው በአምባገነኑ ወያኔ እስር ቤት መታሰራቸውን በመቃወም እና በተጨማሪም አቶ ኦኬሎ አኳይ የኖርዌይ ዜግነት ያላቸውና በኖርዌ ሃገር ይኖሩ የነበሩ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት ከሱዳን በወያኔ የደህንነት ኃይሎች በግፍ ታፍነው መወሰዳቸውንና በወያኔ እስርቤት ታስረው ለሞት ፍርድ መዳረጋቸውን በመቃወም ድምጻችንን  ስናሰማ  ዋልን።

እኛ መነሻቸውን በኖርዌጅያን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደረግን ሲሆን በዛው በኖርዌጅያን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመገኘት የወያኔን ህገወጥ አፈና እና እስራት የሚቃወሙ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝና በማሰማት የተቃውሞ ድምጻችንን አሰምተናል። በስፍራው የነበርን ሰልፈኞች ስናሰሟቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል በጥቂቱ ኦኬሎ አኳዮ ይፈታ፣ ኖርዌይ ዜጋሽ ኦኬሎ አኳዮ የት ነው ያለው?፣ ኦኬሎ አኳዮ አሸባሪ አይደለም የሚሉ የተለያዩ መፈክሮች ይገኙበታል ::

በማያያዝም እኛ የኖርዌ መንግስት ለአምባገነኑ የወያኔ መንግስት የምትሰጠውን እርዳታ እንድታቆምም ጠይቀናል:: በእለቱ የተዘጋጀውን ደብዳቤ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል አማካኝነት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አስረክበዋል። ተወካይዋም ደብዳቤውን ከተቀበሉ በኋላ ጉዳዩ ን እንደሚያዩትና ችግሩ አሳሳቢ ከመሆኑም አኳያ በትኩረት እየተከታተሉት እንደሆነ አሣውቀዋል። 





በመቀጠልም እኛ በቀጥታ ጉዟችንን ወደ እንግሊዝ ኢምባሲ በማቅናት ታላቅ እልህና ቁጣ የተቀላቀለበት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረግን ሲሆን በዛው በእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት በመሆን የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በታላቅ ጩህትና በስሜት ስናሰማቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል Britin were is you citizen, Free Andrgachew Tsige, where is your action, stop discrimination among citizens, we are all Andrgachew Tsige, Brtain dont support terrirost regim in Ethiopia የሚሉት ይገኙበታል:: እነዚሁ በኖርዌ የሚኖሩ ኢትዮጵያ ሰልፈኞች በዚሁ በእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት በመገኘት ባለፈው ጁላይ 3, 2014 ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል::
የዛሬው ሰልፍ ከባለፈው ሰልፍ እጅግ በጣም ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር እኛ በጠቅላላ እኔም አንዳርጋቸው ፅጌ ነኝ የሚል የአንዳርጋቸውን ምስል የያዘ ቲሸርት የለበሱ ሲሆን ለሰልፉም ድምቀትን በመስጠት ለነጻነት ታጋዩ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ያለንን  ፍቅር በአደባባይ ያስመሰከርን ሲሆን የተቃውሙ ሰልፉም በሰልፈኞቹ ቁጣና እልህ የተሞላበት እንደነበር ለማየት ተችሏል::
እኛም  የያዝነውን ደብዳቤ በሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ ተወካይ በአቶ ዳዊት መኮንን በኩል ለእንግሊዝ ኢምባሲ ተወካይ ያስረከቡ ሲሆነ ተወካይዋም ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው፣ በትኩረትና በቅርበት እየሰሩ መሆኑን እንዲሁም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነፃ እስኪወጡ ድረስ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉና ክትትላቸውን እንደሚቀጥሉ ለሰልፈኛው አሳውቀዋል። በመጨረሻም ሰልፈኞቹ በአንድ ላይ በመሆን የግንቦት 7 ህዝባዊ ኃይል መዝሙር ላንቺ ነው ሐገሬ ላንቺ ነው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ላንቺ ነው የሚለውን ህዝባዊ መዝሙር በደማቅና በሀገራዊ ስሜት ዘምረው ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ ከቀኑ 

15፡00 ተጠናቋል።
ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!




Thursday, July 10, 2014

ያማል ግን ይህን እመም ለመቻል ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡

10494588_750671571658261_8784450188684809422_nhabtamu ayalew



የፓርላማ አባልና የአንድነት ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የኢሕአዴግ   መንግስት በሰላም የሚታገሉ ወጣት ፖለቲከኞችን የማሰሩን ጉዳይ እብድነት ብለዉታል።
«እነዚህ ሰዎች አብደው መሆን ይኖርበታል፡፡ ሀብታሙ አያሌውን ፖሊሶች ይዘውት እንደሄዱ ሰማው፡፡ ስልኩ ይጠራል ግን አይመልስም፡፡ የእነርሱን ሃሳብ የሚቃወም ሁሉ አሸባሪ እየመሰላቸው በሽብር እራሳቸውን እያናወዛቸው ያለ ይመሰለኛል፡፡ ሀብታሙን ሊያስሩት ይችላሉ በህዝብ ውስጥ ያለውን የነፃነት መንፈስ ግን ማስረ አይቻላቸውም፡፡ እልፍ አህላፍ የነፃነት ሰዎች ይፈጠራሉ፡፡ ለነገሩ የሚታሰሩ ንፁሃን ታሳሪዎች ሳይሆን አሳሪዎ በከፍተኛ የህሊና ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን መረዳት አሰቸጋሪ አይደለም፡፡» ሲሉ ነበር አቶ ግርማ በፌስ ቡክ አስተያየታቸውን የሰጡት።

«የዚህ ልጅ ነገር ሳያበሳጫቸው አይቀርም፡፡ ሰለማዊ ሰልፍ ላይ በባትሪ አንደሚሰራ ሳያርፍ ያጋልጣቸዋል፡፡ በየሳምንቱ ገበናቸውን በመፅኄት በጋዜጣ ያወጣል፡፡ በዓመት መጨረሻ ደግሞ ትምህርት ተምሮ በክብር በማዕረግ ይመረቃል፡፡ ኢዚህም እዚያም ያገኙታል ሁሉም ጋ ሲያወግዛቸው፤ በቃችሁ ሲላቸው ይሰማሉ፡፡ በቃቸው የሚላቸው ደግሞ እንደበቃቸው ስራቸው ሆኖ ያያቸው እርሱ መሆኑ ያበሳጫቸዋል፡፡ 

ሌላው በግምት አትችሉም ሲላቸው ሀብታሙ ግን አውቃችሀኋለሁ አትችሉም ይላቸዋል፡፡ በእውነት ነርቫቸውን ነው የነካው፡፡ የሚያጓጓው ግን ምን ብለው 28 ቀን የምርመራ ጊዜ ለመጠየቅ አሸባሪ እንደሚሉት ነው፡፡ ዛሬ ቄሱን አሸባሪ አሉ የሚለው ዜና አብርሃ ደሰታ ከመቀሌ ሹክ ብሎናል፡፡ ሀብታሙን ቢሉት አይገርምም፡፡ እንሰማለን፡፡ ተረኞች መዘጋጀት ነው፡፡» ብለው የጻፉት አቶ ግርማ የኢሕአዴግን የፖለቲክ ክስረትና የአቶ ሃብታሙን ታታሪነት የገለጹ ሲሆን፣ እርሳቸዉን ጨምሮ ሌሎች በሰላም የሚታገሉ ሁሉ፣ የሰላማዊ ትግል ለሚያስከፍለው እንዲዘጋጁ ጥሪ አቀርበዋል።

የሰላማዊ ትግል አልጋ በአልጋ እንደሆነ ለሚመስላቸውና በቀላሉ ተስፋ ለሚቆርጡ ወገኖች አቶ ግርማ ሰይፉን ጠንካራ ምክር ለግሰዋል። « ሰላማዊ ታጋዮች መንገላታት እና እስር አሰበውበት የገቡበት ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም ያማል ግን ይህን እመም ለመቻል ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ የሀብታሙ አያሌው ባለቤት ባለፈው ሳምንት አባቷን በድንገት በሞት ተነጥቃለች አሁን ደግሞ ባለቤቷ በግፍ ወህኒ ወርዶዋል ኮልታፋ ህፃን ልጅ ይዛ መከራዋን እንደምትገፋ ሀብታሙ ያውቀዋል፡፡ ሊያሞላቅቃቸው ቢፈልግ ግን ከኢህአዴ ደጅ ፍርፋሪ መልቀም የሚከለክለው አልነበረም፡፡ » ሲሉ ነበር በሰላምዊ ትግል ከአምባገነኖች ጋር ትንቅንቅ የየዙ ወገኖችን ጀግንነት ያስረዱት።

አቶ ግርማ ሲያጠቃልሉ « ውድ የትግል ጓዶች ከዞን ዘጠኝ ወደ ሌላ ዞን መሸጋገራችሁ ቢያሳዝነንም ፅናታችሁ ያበረታናል፡፡ ፅኑ፡፡ ለካ እነርሱ ይህን የማንበብ መብት የላቸው፡፡ በዞን ዘጠኝ የምትገኙ ሁሉ በርቱ ፅናቱን ይስጣችሁ ማለት የግድ ይላል» በማለት ትግሉን ከማፋፋም ዉጭ ሌላ አማራጭ እንደሌልም ለማሳየት ሞክረዋል።

መንግስታዊ ሽብርተኝነትን የሚሸከም ትከሻ አይኖረንም!!!


THURSDAY, JULY 10, 2014


ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም

የህወሓት/ኢህአዲግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ዜጎችን በማፈንና በማሰቃየት ብሎም በመግደል የአፈና አገዛዙን ለረጅም ጊዜ ሲያራምድ መቆየቱ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማፈን እስራትና ግድያውን ህጋዊ ለማስመሰል የተለያዩ አፋኝ አዋጆችን አውጥቷል፡፡ እነዚህን አዋጆችንም ተገን አድርጎ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባለትን፣ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማት መሪዎችን እና በአገዛዙ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ማሰሩን፣ ማሰቃየቱንና ግድያውን ተያይዞታል፡፡ በህገ መንግስቱ የተካተቱ የሰብዓዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በሙሉ የሚጥሰውና የአምባገነንነት ስልጣኑን ለማራዘም ሲል ያፀደቀው የፀረ-ሽብር አዋጅ ከፀደቀበት እለት አንስቶ ኢህአዴግ ለስልጣኔ ያሰጉኛል የሚላቸውን ፍፁም ሰላማዊ ታጋዮችንና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በድፍረት የፃፉ ጋዜጠኞችን ብሎም የእምነት ነፃነታችን ይከበር ብለው የጠየቁ የሀይማኖት መሪዎችን በጠራራ ፀሃይ ያለምንም ወንጀል በዚሁ ህገ ወጥ አዋጅ ‹‹የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል›› በሚባል ማንነቱ በማይታወቅ የጨለማ ቡድን ወደ እስር ቤት እያጋዘ ይገኛል፡፡

ይህን የሚያጋልጡ ሚዲያዎችንም ለማፈን እስር ቤቶችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያፈሰሰ የአየር ሞገድ ያውካል፤ በዚህ ሳያበቃ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ፖለቲከኞችን ለማሸማቀቅ እንደ ኢሳት ያሉ ሚዲያዎችን የአሸባሪ ልሳን ብሎ በመፈረጅ ሚዲያውን የሚጠቀሙትን ደግሞ ከአሸባሪዎች ጋር ንክኪ እንዳላቸው አድርጎ መወንጀሉን ቀጥሎበታል፡፡ እንደሰማያዊ እምነት ማንም አካል መልእክት የሚያስተላለፍበትን የሚዲያ ተቋም ሊመርጥለት እንደማይችል መንግስት እንዲገነዘበው ከዚህ በፊት በግልፅ ያሳወቀ ሲሆን አሁንም ፓርቲው በዚሁ የፀና አቋሙ እንደሚቀጥል በድጋሚ ይገልፃል፡፡

ባጠቃለይ የዚህን ገዢ አካል የእውር ድንብር ሀገር የማስተዳደር ጉዞ ለመታገል በርካቶች በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም በህወሓት/ኢህአዲግ ግፍና መከራ ተገፍተው ስርዓቱን በሃይል እናስወግዳለን ብለው ሀገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የህወሓት/ኢህአዲግ ማናለብኝነትና የስልጣን ጥመኝነትም በግለሰቦች ላይ ከሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ በላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋትን አስከትሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ይህ ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ስርዓት የሀገሪቷን ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር በማጥበብ ሀገራችንን ወደ አልተፈለገ አለመረጋጋትና ቀውስ እየመራት ይገኛል፡፡ፓርቲያችንም እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም በቅርቡ እየተፈፀሙ የሚገኙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ስላሳሰበው ይህን መግለጫ ለማውጣት ተገዷል:-

1. ሰኔ 16 2006 ዓ.ም የየመን መንግስት የዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን በመጣስና በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ በመግባት የአማፂ ቡድን ግንቦት ሰባት ዋና ፀሃፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዟ ይታወሳል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለህወሓት/ ኢህአዴግ ተላልፈው መሰጠታቸውን ከ16 ቀናት በኋላ መታወቁና ይህንንም ሁለቱ ሀይሎች ማመናቸው ተሰምቷል፡፡ ነፃነት በሌለበት ሀገር ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት የሌሎች ሀገር መንግስታት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በተለይ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጥላ የሚያጠላ መሆኑን ግንዛቤ አለመወሰዱ እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከተያዙ በኋላ ላለፉት 16 ቀናት በምን አይነት ሁናቴ እንደቆዩ ህዝብና ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁት አለመደረጉ፤ ስለ አያያዛቸው ሁኔታም በማህበረሰቡና በፓርቲያችን ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲኖር አድርጓል፡፡ሰማያዊ ፓርቲ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሰብዓዊ አያያዝ እያሳሰበው ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ አገዛዝ አያያዛቸውን ግልፅ እንዲያደርግ ሰብዓዊ ክብራቸውም እንዲጠበቅ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
2. በዚሁ ሳምንት ገዢው ፓርቲ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የአምባገነኑን መንግስት ህወሓት/ኢህአዲግን ሲታገሉ የነበሩ ፖለቲከኞችን በስመ አሸባሪ ከያሉበት እየለቀመ ህገ-ወጥ እስራት መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ ህወሓት/ኢህአዲግ ይህ ግብታዊ ተግባሩ ምንም እንኳን አዲስ ባይሆንም በአሁኑ ወቅት ለውጥን ለማምጣት በቆራጥነት እየታገሉ ያሉ ሰላማዊ ታጋዮችን ማሰሩ በሀገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎችን ከአማፂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው በማስመሰል ሰላማዊ ትግሉን ለማዳከምና መጪውን 2007 ዓ/ም ምርጫ ያለ ተቀናቃኝ ለማለፍ የሚደረግ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የፓርቲያችን ብ/ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነው አቶ የሺዋስ አሰፋ በሰላማዊ ትግሉ በቁርጠኝነት እየተሳተፈ ባለበት ሁኔታ ለእስር መዳረጉ፤ የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፤ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄን በመፍጠር ላይ ያለው የአረና /ትግራይ/ ፓርቲ አመራር አባል የሆኑትን አቶ አብረሃ ደስታ ለእስር መዳረጋቸው ህወኃት/ኢህአዴግ የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል፡፡ በመሆኑም አገዛዙ እያካሄደ ያለውን መንግስታዊ ሽብር አቁሞ ለሀገርም ሆነ ለራሱ የሚበጀውን መንገድ እንዲከተል እያሳሰብን የታሰሩት የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም ፓርቲያችንን መንግስት እያደረገ ያለው ሽብርን የመንዛትና ህግን የመጣስ ተግባሩ መቼም ቢሆን ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያቆመውና ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአፅንኦት እየገለፀ እነዚህንና ከላይ የተጠቀሱትን የገዢውን ፓርቲ መርህ አልባነት፣ ህገ-ወጥነት እና የለየለት አምባገነንነትን አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አጣምሮ የትግል ስልቱን ደረጃ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳለበት አምኗል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ለምናደርጋቸው ሀገር አቀፍ ንቅናቄዎች መላው የሀገሪቱ ህብረተሰብ በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን እያስተላለፈ ለዚህም ቁርጠኛ አመራር ለመስጠት ዝግጁነቱን ለመግለፅ ይወዳል፡፡በዚህ አምባገነንነትን ለመታገል በሚደረገው ንቅናቄም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ህጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች፤አለም አቀፍ ተቋማት፤የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ሲቪክ ማህበራት፤መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሰላማዊ ትግሉ ጎን በጋራ እንድንቆም እንጠይቃለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሰማያዊ ፓርቲ
ሀምሌ 3/2006ዓ/ም

Sunday, July 6, 2014

ሚስስ አና ጎሜዝ፣ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ማረጋገጣቸውን ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊልያም ሔግ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡




የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑትና የኢትዮጵያን መንግሥት በመንቀፍ የሚታወቁት ሚስስ አና ጎሜዝ፣ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ማረጋገጣቸውን ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊልያም ሔግ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
ሚስስ ጎሜዝ በይፋዊ ድረ ገጻቸው ባሰፈሩት ደብዳቤ አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ መረጃ ማግኘቻቸውን ገልጸው፣ በዚህም መደንገጣቸውንና የእንግሊዝ መንግሥት ምንም ዓይነት ዕምርጃ ባለመውሰዱ መናደዳቸውንም አስረድተዋል፡፡
ሚስ ጎሜዝ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የሕይወትና የአካል አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል፣ እንዲሁም ባላመኑበትና ባልፈጸሙት ወንጀል ክስ ሊቀርብባቸው እንደማይገባ ገልጸው፣ በተቻለ መጠን ወደ እንግሊዝ የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል፡፡
በ1997 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት ሚስስ ጎሜዝ፣ የእንግሊዝ መንግሥት የኢትዮጵያ ዋነኛው ለጋሽና የፖለቲካ ደጋፊ በመሆኑና ተፅዕኖውም ከማንም አገር የላቀ በመሆኑ፣ አቶ አንዳርጋቸውን ማስፈታት አለበት ሲሉ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፕሮግራም መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ተሰጥተዋል መባሉን በተመለከተ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጡም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የሚፈለጉ በመሆናቸው ተላልፈው መሰጠት እንዳለባቸው ለውጭ ሚዲያ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ኢትዮጵያና የመን በ1991 ዓ.ም. በተፈራረሙት የፀጥታና የደኅንነት ስምምነት መሠረት፣ የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ አሳልፋ እንደምትሰጥ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል የእንግሊዝ ዜግነት ስላላቸው ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠት የለባቸውም የሚሉ ሲኖሩ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እስከገቡ ድረስ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የሚከራከሩ አሉ፡፡