Tuesday, February 11, 2014

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ 100 ሺህ በላይ የኖርዌይ ክሮነር በሳውዲ ለተጎዱት ወገኖቻችን አዋጡ

በሳውዲ አረብያ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጉዳት በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን በሳውዲ ኢምባሲዎች ፊት ለፊት ሲገልፁ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።ይህ ሁኔታ ከቁጭት ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ ለተመሰረተው ''አለም አቀፍ ህብረት ለኢትዮጵያውያን መብት በሳውድ አረብያ'' (Global Alliance for the Rights of Ethiopians in Saudi Arabia) በኩል ለአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (International Organization for Migration - IOM) የሰበሰቡትን ገንዘብ ሰጥተዋል።ለምሳሌ ባለፈው ወር በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያሰባሰቡትን በድርጅቱ በኩል ለ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) 30 ሺህ ዶላር አስረክበዋል። http://abbaymedia.com/2014/02/05/washington-dc-fundraising-for-ethiopian-migrants-displaced-from-saudi-arabia/  
ትናንት የካቲት 2፣2006 ዓም  በኦስሎ ከሳውዲ አረብያ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን መርጃ የሚሆን የገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተዘጋጅቶ ነበር። ማኅበርሰቡ ከተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በተውጣጡ ኮሚቴዎች አማካይነት ከትኬት ሽያጭ እና በኖርዌይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ100 ሺህ በላይ የኖርዌይ ክሮነር ( ከ 300 ሺህ ብር በላይ) ለማሰባሰብ ችሏል።

የትናንቱ የኦስሎ ዝግጅት የአለም አቀፉ የኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ አካል ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ እና ዝነኛዋ የመድረክ ሰው እና ጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን ተገኝተዋል።

ገሊላ መኮንን የኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ እና ለወገን ደራሽነታቸው እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ገልፃ በእዚሁ በጎ ተግባራቸው ጠንክረው እንዲቀጥሉ አሳስባለች።ቀጥላም  የሳውዲ አረብያውን ጉዳይ ኢትዮጵያውያን እንዲያውቁት ያደረገው የኢሳት አካል መሆኗ የሚያኮራት መሆኑን ስትገልፅ ከተሳታፊው ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተቸሯታል።
 በዝግጅቱ ላይ የታደሙት ሌላው እንግዳ የአዲስቱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ ነበሩ።አቶ ኦባንግ  ግልፅ እና ከልብ የመነጨ ሃገራዊ ፍቅር በምነበብበት ንግግራቸው ውስጥ ከተናገሩት የሚከተሉት ይገኙበታል-


''የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሰው አልገደለም።ኢትዮጵያዊነት መከበር ያለበት ነው''
''እኛ ድሃ አይደለንም በተፈጥሮ ሀብት፣በውሃ በሁሉ ሃብታም ነን።ደንቆሮም አይደለንም ብዙ የተማሩ ሰዎች በመላው አለም አሉ…..ነፃነታችንን ተባብረን ማግኘት አለብን…ነፃነታችንን ከራሳችን መጀመር አለብን'' ካሉ በኃላ
በመጨረሻ እንዲህ አሉ '' እኛ ስንሰቃይ አሜሪካ ዝም ብላ ይሆናል፣የአውሮፓ ህብረት ምንም አላለ ይሆናል የኢትዮጵያ አምላክ ግን ከእኛ ጋር ነው ያለው''

በእዚህ ዝግጅት ላይ የኢህአዲግ/ወያኔን አንድ ለአምስት የመጠርነፍ ስታሊናዊ ተግባር የሚያሳይ ሙዚቃዊ ድራማ እና በሳውዲ አረብያ የሚኖሩ እህቶቻችንን ሕይወት የዳሰሰ ትረካን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል::
ጉዳያችን ጡመራ

No comments:

Post a Comment