ነገረ ኢትዮጵያ) የአውሮፓ ህብረት ዛሬ መጋቢት 1/2007 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ጽ/ቤቱ ባደረገው ስብሰባ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በተጋባዥ እንግዳነት ተገኝተው ከህብረቱ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ ያላቸው 20 ያህል የህብረቱ አባል አገራት በተገኙበት ስብሰባ ላይ አብዛኛዎቹ በአምባሳደሮቻቸው እንዲሁም ቀሪዎቹ በምክትል አምባሳደሮቻቸው ተወክለው የተገኙ ሲሆን
ተወካዮቹ ወቅታዊ የምርጫ ሂደት እንቅስቃሴና የሰማያዊን የምርጫ እንቅስቃሴ፣ በምርጫው ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች፣ የፓርቲው አማራጭ ፖሊሲዎች፣ የድርጅቱን ጥንካሬ፣ የአንድነት አባላት ወደሰማያዊ መምጣታቸው ለትግሉ የሚኖረው ትርጉምና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ሰማያዊ ፓርቲ ከ200 በላይ ዕጩዎች በህገ ወጥ መንገድ እንደተሰረዙበት፣ የፓርቲው የቅስቀሳ መልዕክቶቹ ከ6 ጊዜ በላይ በሚዲያ እንዳይተላለፍ መከልከሉን፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ድብደባ፣ እስራትና ወከባ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው በምርጫ ሂደት ኢህአዴግ አፋኝነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የአንድነት አባላት ሰማያዊን መቀላቀላቸው ትግሉን እንደሚያጠናክረው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአንድነትና መኢአድ ላይ የተፈፀመው ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን እንዲሁም ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በኃይል እያጠፋ ‹‹ከእኔ ውጭ አማራጭ የለም›› የሚል አቋሙን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳየት እንደሚፈልግ ለህብረቱ ተወካዮች አስረድተዋል፡፡ ‹‹የአውሮፓ ህብረት ችግር የኢትዮጵያን ችግር በአውሮፓውያን ተቋማትና የስነ ልቦና ልክ ማየቱ ነው›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል የአውሮፓ ህብረት ‹‹የተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲያቸው ምንድን ነው?›› በሚል የሚያነሱትን ተደጋጋሚ ጥያቄ አስታውሰው መደረጀትና መናገር ያልቻለውን የኢትዮጵያን ህዝብ በአውሮፓ ተቋም አይን አይቶ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ማንሳቱ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ብዙም እርባና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በእኛ አገር የፖለሲ አማራጭ ለማቅረብ አይቻልም፡፡ ሚዲያው በገዥው ፓርቲ የተያዘና የተቃዋሚዎችን ሀሳብ የማያስተናግድ ዝግ ሆኗል፡፡ እናንተ እንደምትገምቱት የፖሊሲ አማራጭ ለማቅረብ አመች ሁኔታዎች ቢኖሩ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ የተሻለ ምሁርራንና ሀሳብ ስላላቸው ዝርዝር ፖሊሲያቸውን ለማቅረብ አይቸገሩም ነበር፡፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ኢህአዴግ ‹‹ተቃዋሚዎች የተበታተኑና የተዳከሙ በመሆናቸው ለቀጠናው ሰላም አማራጩ እኔ ብቻ ነኝ›› ብሎ የአውሮፓ ህብረትን እንደሚያታልል የገለጹት ኢ/ር ይልቃል ‹‹ኢትዮጵያውያን ካላቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ማየት ስላልቻላችሁ ኢህአዴግ እያታለላችሁ ነው፡፡ እናንተም ለመታለል ዝግጁ ሆናችኋል፡፡›› ሲሉ የአውሮፓ ህብረትን ወቅሰዋል፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39600#sthash.ligw7lv8.dpuf
No comments:
Post a Comment