
.
«አንድ ድርጅት የፖለቲካ ተቃውሞውን ቢገልጽ ፣ ከአስተሳሰቡ ጋር ባንስማማም እንኳ ከለላ እንሰጠዋለን፣ ይሄ በአሜሪካ በሌላም ቦታ የሚሰራበት እውነታ ነው፤ ይህን ማድረግ ለዲሞክራሲ እድገት አስፈላጊ ነገር ነው» ያሉት ኦባማ ፣ ድርጅቶቹ ወደ ሃይል ሲያዘነብሉና በህገመንግስት የተቋቋመን መንግስት ለመገልበጥ ሲሞክሩ፣ ድርጊቱ ያሳስበናል።» በማለት መልሰዋል። የውጭ አገር ጋዜጠኞች ፣ በእስር ላይ ስለሚገኙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እንዲሁም ስለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ለፕ/ት ኦባማና ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ፕ/ት ኦባማ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በዲሞክራሲ ዙሪያ ከአቶ ሃይለማርያም ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን፣ አሜሪካ በቅርብ ሁና እገዛ ለመስጠት መዘጋጀቷን ገልጸዋል። የኢህአዴግ መንግስት ከፕ/ቱ ጉብኝት በዋናነት የሚጠብቀው ለስልጣኑ ስጋት የሚፈጥሩ ድርጅቶች በሽብረተኝነት እንዲፈረጁለት ቢሆንም፣ ይህንን ሳያገኝ ቀርቷል። ይሁን እንጅ ባራክ ኦባማ የኢህአዴግን መንግስት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ ነው ማለታቸው በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ሳያስቆጣ አይቀርም። ኦባማ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ እየጠበበ ስለመጣው የፖለቲካ ምህዳር ሲናገሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ የሚል ካባ ማልበሳቸው፣ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲን ተቃርኖ የሚያሳይ ነው።
.
በሌላ በኩል ኢ/ር ይልቃል ለፕሬዝደንት ኦባማ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ እንደማይገኙ አስታውቀዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት መንግስት ሀምሌ 20/2007 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ሰዓት ላይ ቤተ መንግስት ውስጥ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የሚያደረገውን የእራት ግብዣ ያልተቀበሉት፣ «አሸባሪ አድርጎ የሚቆጥረን ኢህአዴግ፣ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሲመጡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ለማስመሰልና ዕውቅና ለማግኘት ያደረገው በመሆኑ አልገኝም» ብለዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል አክለውም «የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና እና ስቃይ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ የጠራው የቅንጦት ግብዣ ላይ መገኘት የህዝቡን ሰቆቃ እንደመርሳት እቆጥረዋለሁ» ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ማለታቸው ቅር እንዳሰኛቸውም ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ «ኢህአዴግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ማለት የሰላማዊ ታጋዮችን ስቃይ የሚክድና ለአምባገነኖች ይሁንታ የሚሰጥ ነው» ሲሉ የፕሬዝደንት ኦባማን ንግግር ነቅፈውታል፡፡ ፕሬዝደንት ኦባማ የጠበንጃ ትግልን አለመደገፍን ለመግለፅ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ ተቋማት ኢ-ዴሞክራሲያዊ መሆኑን አረጋግጠውት፣ መቶ ፐርሰንት ምርጫ አሸንፌያለሁ የሚልን ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደተመረጠ መግለፃቸው እንዳሳዘናቸው ኢ/ር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment