ሰኔ 10፣2009 ዓም
==============
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ቅዳሜ ሰኔ 10፣2009 ዓም በኦስሎ፣ኖርዌይ የኢትዮጵያ
አገራዊ ንቅናቄ ጉባኤ ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጋብዞ ጉባኤ አካሂዶ ነበር።ይሄው በኦስሎ የቀይ መስቀል ዋና መስርያ
ቤት አዳራሽ የተካሄደው ጉባኤ ላይ ከ200 ሰው በላይ የታደመበት ነበር።በጉባኤው ላይ የተጋበዙት የአርበኞች
ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ።
የዝግጅቱን መክፈቻ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሰብሳቢ አቶ ይበልጣል ጋሹ በንግግር ከተከፈተ በኃላ የመጀመርያ ተናጋሪ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ።
አቶ ሌንጮ "ተቀምጨ እንዳልናገር አጭር ነኝ" በሚል ቀልድ አዘል ንግግር ተሰብሳቢውን ፈገግ ካስደረጉ በኃላ
የመተባበር አስፈላጊነት ላይ አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል።በመቀጠልም " በ1966 ዓም ንጉሱ ከስልጣን ሲወርዱ
እርሳቸው ይወረዱ እንጂ መጪው ጊዜ የተሻለ እንደሆነ በጣም ተስፋ አድርገን ነበር። ካሉ በኃላ ሆኖም ግን ደርግ መጣ
ብለዋል።
አቶ ሌንጮ አያይዘውም ደርግ ሲመጣ ከደርግ የባሰ ሊመጣ አይችልም ብለን ስናስብ የባሰ መጣ።ሆኖም ግን ማሰብ
የሚገባን ደርግ ሲገድል በቀጥታ `የፍየል ወጠጤ` እያለ ነበር።ስለሆነም የገደለውን ቁጥር መገመት ይቻላል።የአሁኖቹ
ግን በስውር ነው።በስውር ያሰሩት፣የገደሉት እና የሰወሩት ሕዝብ ቁጥር አሁን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ሁሉን
በድብቅ ነው የሚያደርጉት" ካሉ በኃላ ስለመጭዋ ኢትዮጵያ ማሰብ እንደሚገባ እና እርሳችውንም የሚያሳስባቸው ጉዳይ
መሆኑን ጠቅሰዋል።ለዚህም የሱማሌ፣ደቡብ ሱዳን ጉዳይ እያነሱ በሰፊው ለማብራራት ሞክረዋል። አቶ ሌንጮ ኢትዮጵያ
እስካሁን እንደ ሀገር እንድትቆይ ካደረጋት ጉዳይ ውስጥ ቀዳሚው ያሉት የህዝቡ ጨዋነት መሆኑን ሲናገሩ እንዲህ አሉ -
"ኢትዮጵያን እስካሁን ጠብቆ ያኖራት የህዝቧ ጨዋነት እንጂ የመሪዎቿ ብቃት አይደልም" ነበር
ያሉት።በመቀጠልም አቶ ሌንጮ አሁን ያለው መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ሕዝቡም ትኩረት የማይሰጠው ጉዳይ
የህዝብ ቁጥር መጨመር እና እርሱን ተያይዞ የሚመጣው የአካባቢ ብክለት፣ የማህበራዊ ኑሮ መዳከም እና የህዝብ ኑሮ
ማሽቆልቆል ዋነኞቹ ችግሮች ውስጥ እንደሚካተት አብራርተዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል
በመቀጠል ንግግር ያደርጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ነበሩ።ፕሮፌሰሩ ንግግራቸውን
የጀመሩት ሶስት ነገሮችን በቅድምያ ካላወቅን ነገን ለማወቅ ያስቸግረናል በሚል መነሻ ነጥቦች ነበር። እነርሱም : -
1/ አሁን የገጠመን ባላንጣ (የወያኔ ስርዓት) ብሔራዊ ጥቅም የሚባል ነገር የማያውቅ፣ ስርዓቱ ስልጣኑን የማያስጠብቅበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሁሉ ነገር እንዲወድም የሚሰራ ስርዓት መሆኑን፣
2/ የሀገራችን ፖለቲካ በብዙ ምክንያቶች ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ያለ መሆኑ እና
3/ የህዝባችን የሞራል ደረጃ እየወረደ መምጣቱ የሚሉት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች የአገር አድን ንቅናቄው መፍትሄ መሆኑን ለማመላከት ንቅናቄው እንዴት ችግሮች ይፈታሉ ብሎ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ለመሆኑ የአገር አድን ንቅናቄው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የሚሰጣቸው ስልታዊ ምንድን ናቸው? በሚል በጥያቄ
ንግግራቸውን የቀጠሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ንቅናቄው በሚከተሉት ስልታዊ መንገድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የመፍታት
አቅም እንዳለው አብራርተዋል።
1/ በሚደረጉ የንቅናቄው ውይይቶች መጥራት የሚጎዳላቸው የሃጋራችን የፖለቲካ ችግሮች እንዲጠሩ በማድረግ፣
2/ በውይይቱ ሂደት መስማማት።በሂደቱ ላይ ከተስማማን በውጤቱ ላይ መስማማት መጨረሻ የሚመጣ ጉዳይ ነው። አሁን
የውይይቱ ሂደት ዲሞክራሲያዊ መሆኑ ላይ መስማማት እና ውጤቱን ደግሞ ሕዝብ እንዲወስን መተው ነው።
በዲሞክራሲ ሂደት ላይ ከተስማማን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ልዩነት አይኖርም ማለት አይደለም።ለምሳሌ በኢኮኖሚ ጉዳዮች
ላይ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ የግድ ላንስማማ እንችላለን። ሆኖም ግን የቀሪ ልዩነታችን መፍቻ ዲሞክራሲያዊ
አፈታትን ስለመረጥን ብዥታ አይኖርም ማለት ነው።
ለጨረታ የቀረበው እና ከበርገን ከተማ የመጡ የጉባኤ ታዳሚዎች በ13 ሺህ የኖርዌይ ክሮነር የወሰዱት ስዕል
ከእዚህ በተጨማሪ የጋራ ንቅናቄው ምን እያደረገ ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሲያስረዱ አገራዊ ንቅናቄው -
ሀ) ዋና ጉዳዮች ላይ ማትኮር መቻሉ ፣
ለ) ሌሎች ድርጅቶችን እያሰባሰበ ወደ አንድ ነጥብ ማምጣት ላይ እየሰራ መሆኑ፣
ሐ) ድርጅቶችን ማቀፉ የትግሉን መልክአ ምድራዊ ሽፋን ማስፋቱ እና አገራዊ ቅርፅ መያዙ፣ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት የንቅናቄው ተግባራት በምሳሌ ካስረዱ በኃላ የወያኔን ውድቀት ለማፋጠን የሚያስፈልጉ ሶስት አበይት ጉዳዮችን ጠቅሰዋል። እነርሱም -
1ኛ) የጠራ መንገድ በትግሉ ሂደት መያዝ፣
2ኛ) መሬት የያዘ ትግል ማካሄድ እና
3ኛ) ወያኔ ያዳከመብንን ሞራላዊ ልዕልና መልሰን መገንባት እና ማምጣት የሚሉ ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አበይት ጉዳዮች ውስጥ የሞራል ልዕልናችንን መልሰን መገንባት የእረጅም ጊዜ ስራችን መሆን
ያለበት ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ግን በፍጥነት የሚሰሩ እና አሁን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች መሆናቸውን አውስተዋል።
በእዚሁ ጉባኤ ላይ ከነበሩት የፕሮፌሰር ብርሃኑ እና አቶ ሌንጮ ንግግሮች በተጨማሪ የጥያቄ እና መልስ መርሃ ግብር
ነበር።በጥያቄ ከተነሱት ውስጥ አሁን ያለነው ወጣቶች በወያኔ ዘመን ያደግን ስለሆነ ስለ ጎጥ እየሰማን ስላደግን
ኢትዮጵያዊ ስሜታችን ሳይጎዳ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ´አለብን? የሚል የነበረ ሲሆን አቶ ሌንጮ ሲመልሱ -
"በኢትዮጵያ ታሪክ ማንም ንጉስ ከእዚህ ብሔር የመጣሁ ነኝ ብሎ አያውቅም።በኢትዮጵያም ጨቋኝ የሚባል ብሔር
የለም።የጨቆነ ከአንድ ብሔር የወጣ ቡድን ቢሆን ይህ ቡድን ብሄሩን ይወክላል ማለት አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።"
ብለዋል።በመጨረሻም አቶ ሌንጮ " እኔ ኦሮሞም ኢትዮጵያዊም መሆን እፈልጋለሁ።" ብለዋል። በማስከተልም ፕሮፌሰር
ብርሃኑ ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያዊው ወጣት ትውልድ ውስጥ ወጥቷል የሚል ፈፅሞ ግምት እንደሌላቸው እና ለእዚህም
በርካታ ማስረጃዎች መኖራቸውን አብነት እየጠቀሱ አስረድተዋል።
በመጨረሻም በዋናነት የፕሮፌሰር ብርሃኑን እና አቶ ሌንጮ ለታን ንግግር፣ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መመለስ፣የገቢ
ማሰባሰቢያ ጨረታ የተካሄደበት ጉባኤ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ እንግዶችን በክብር በመሸኘት ተፈፅሟል።ባጠቃላይ በእዚህ
ጉባኤ ላይ የታየው ከፍተኛ ዲስፕሊን፣የሰዓት አጠቃቀም እና የመድረክ መስተንግዶ ሁሉ የተዋጣለት እና ደረጃውን
የጠበቀ መሆን የጉባኤውን ተሳታፊዎችንም ሆነ እንግዶችን ያስደሰተ ተግባር ሆኖ አምሽቷል።
No comments:
Post a Comment