ኢ/ር ይልቃል ከደጋፊዎቻቸውና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጋር ይወያያሉ
ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ሚኒልክ ያረፉበትን መቶኛ አመት ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር የገለፁ ሲሆን፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ትናንት ወደ ጀርመን በማቅናት ከፓርቲው ደጋፊዎችና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ይወያያሉ ተባለ፡፡ አፄ ምኒልክ ያረፉበትን መቶኛ ዓመት ለመዘከር በሚዘጋጅ የፓናል ውይይት፣ በምኒልክ ዙሪያ የኢትዮጵያ ምሁራን የጥናት ጽሑፍ እንደሚቀርብ የገለፁት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው በጽሑፎቹ ዙሪያ ሌሎች የአፍሪካ ምሁራንም ይወያያሉ ተብሏል፡፡ እንጦጦ የሚገኘው የምኒልክ ቤተ መንግስትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአፄ ሚኒልክ ፋውንዴሽን የሆነውና ባዕታ ማሪያም አጠገብ የሚገኘው የካህናት ማሰልጠኛና የአረጋዊያን መርጃ እንደሚጐበኙም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ አፄ ምኒልክ በዘመናቸው ምን ዓይነት መሪ እንደነበሩ የሚያሣይ የፎቶ ኤግዚቢሽን በፓርቲው ጽ/ቤት እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡ ፓርቲው፣ የአፄ ምኒልክን ህልፈት መቶኛ አመት ለመዘከር ለምን እንደፈለገ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ፣ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ጋር ከማስተዋወቃቸውም በተጨማሪ በአድዋው ጦርነት ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳዩ ቆራጥ መሪ ናቸው ብለዋል፡፡ “በእርሳቸው ዘመን ቴክኖሎጂ እንደ ሰይጣን ይቆጠር ነበር” ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ከካህናቱና ከቀሳውስቱ ጋር እየተሟገቱ ታላቋን ኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ ቀመስ በማድረጋቸው ሊዘከሩ ይገባል ብለዋል አፄ ሚኒልክ በወቅቱ ባቡር፣ ስልክ፣ መኪና፣ ፖስታ፣ ሆቴልና ባንክ በመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ህዝባቸውን ተጠቃሚ አድርገዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ “ዛሬ ስለ ባቡርም ሆነ ስለአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ልማት ስናወራ ቅድሚያ መታወስ ያለባቸው አፄ ሚኒሊክ ናቸው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል በውጭ አገራት ከሚገኙ ደጋፊዎች በቀረበላቸው ግብዣ ትላንትና ወደ ጀርመን መጓዛቸውን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡ በሁለት ሳምንታት የጀርመን ቆይታ፣ ኢ/ር ይልቃል በሶስት የአገሪቷ ከተሞች ከደጋፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የገለፁ ሲሆን፤ ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመወያየት ፕሮግራም ተይዞላቸዋል ብለዋል - አቶ ብርሃኑ፡፡ ኢ/ር ይልቃል ወደ አሜሪካ በማምራት በሰባት ስቴቶች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታና የፓርቲውን እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ደጋፊዎችን እንደሚያደራጁ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment