Monday, January 26, 2015

የኢትዮጲያ ፖለቲካ መልኩን የሚቀይርበት 11ኛው ሰዓት ላይ ደርሷል!

By: Daniel Fikre

መግቢያ መውጫ አሳጥቶ፤ የወንድ በር እንኳን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን በማን አለብኝነትና በትምክህት ስነልቦና ተወጥሮ በአፈና ጅራፉ ሲገርፈን ፀጥ ብለን የምናይበት የፈሪ ልብ፤ መጠን ያለፈውን የጭቆና ቀንበር የምንሸከምበት ጫንቃ የለንም፡፡
ጋዜጠኛ ስለሺ የተደበደበው ሰውነቱ በፋሻ ተጠቅልሎ ይታያል
ጋዜጠኛ ስለሺ የተደበደበው ሰውነቱ በፋሻ ተጠቅልሎ ይታያል
አዎን ኢህአዴግ የደም መስዋዕትነት የከፈልኩበትን ስልጣን በቀላሉ አለቅም በሚል የሞት የሽረት ትግል እንደሚያደርግ ሁሉ እኛም ጓዶቻችን የታሰሩበትን ትግል እና ፓርቲ ወደጎን ትተን የትም አንሄድም፡፡ አንዱአለም አራጌ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሀ ደስታ፣ አግባው ሰጠኝ እና ሌሎቹም የታገሉለትን አላማ ከግብ ሳናደርስ ወደኋላ ማለት የለም፡፡
ትግሉ ሰላማዊ እና ሰላማዊ ብቻ እንዲሆን ከአንድ ወገን ብቻ (ከተቃዋሚዎች በኩል) እየተደረገ ያለውን ጥረት ኢህአዴግ እንደፈሪነት እየቆጠረው በትዕቢት ተወጥሮ ያስራል ይገላል፡፡ ነገም ኢህአዴግ ከዚህ የተለየ ነገር አያደርግም፡፡
ፓርቲያችን አንድነትን ለጀሌዎችህ ስትሰጣቸው እጃችንን አጣጥፈን ዝም ብለን አናይህም በሚል ነገ የአንድነት አባላቶች እና ደጋፊዎች ሰልፍ ሲወጡ ወያኔ እንደለመደው ያስራል፡፡
ዛሬ በልሳኑ ኢቲቪ/ኢቢሲ ደግሞ ሰማያዊ ምርጫው ሰላማዊ እንዳይሆን እሰራለሁ አመፅንም እጠራለሁ ብሏል ሲል በሬ ጥጃ ወለደ ዲስኩሩን ደስኩሯል፡፡
አንድነትን ለእነ ትዕግስቱ አወሉ ሰጥቼ እውነተኛ አመራሮቹንም አስሬ አፈርሰዋለሁ፤ ሰማያዊን ደግሞ አመፅ ሊጠራ ነው በሚል ፓርቲውን አግዳለሁ አመራሮቹንም አስራለሁ በሚል ስሌት እየሰራ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልፅ ሆኗል፡፡
እንግዲያው ፓርቲዎችን ከዘጋ፣ ህጋዊ አመራሮችንም ካሰረ እና ሰላማዊውን መንገድ ከዘጋው የኢትዮጲያ ፖለቲካ መልኩን ይቀይራል፡፡
ጓዶቹ የታሰሩለትን ፓርቲ፣ አላማ እንዲሁም ትግል ወደጎን ትቶ የሚሄድ የለምና አሁን ትግሉ ሞትን ፊት ለፊት የመጋፈጥ እና ነፃነትን የመሻት ነው፡፡ ‹‹የሰላም በሮች ሲዘጉ የአብዮት በሮች ይከፈታሉ›› እንዲል ጋዜጠኛው ነቢዩ፡፡

No comments:

Post a Comment