እጅግ በርካታ ዝግጅቶች በተጨማሪ ከግንዛቤ ሊያስገባቸው የሚገቡ 10 ነጥቦች መዘርዘር ነው። ምርጫው ነፃ
እና ፍትሃዊ ካልሆነ ከምርጫ መወጣት (ቦይኮት ማድረግ) ጠቃሚ ነው ለሚሉ ወገኖችም መልስ ይሰጣል
ይኽ ጽሑፍ። መልካም ንባብ።
(1) መንግስት በስልጣን መኖር የሚችለው፥ (ሀ) ህጋዊነት የሚለግሰው ህዝብ ሲኖር፣ (ለ) ህዝብ የሙያ
ትብብር ሲለግስ፣ (ሐ) ህዝብ የግብር ክፍያ ትብብር ሲያደርግ፣ (መ) የመንግስትን የአገር ተፈጥሮ ሃብት
እና አገራዊ ኢኮኖሚ ባለቤትነት ህዝብ እሺ ሲል ብቻ ነው። እነዚህን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ህዝብ
አሳልፎ ለገዢው ቡድን አሳልፎ የሰጠው በፍራቻ ወይንም በፈቃደኛነት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ
የእነዚህ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ባለቤት ህዝብ ነው።፡ ስለዚህ ነው የመንግስት ስልጣን ምንጭ ህዝብ
ነው የሚባለው። ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት ነው የሚባለውም ስለዚህ ነው። ስለዚህ የመንግስት
ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ የመንግስት ስልጣን ለመለገስ የተሳተፈባቸው ምርጫዎች ህገወጥ ሊሆኑ
አይችሉም። ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች የመንግስት ስልጣን ባለቤት ባለመሆናቸው እራሳቸውን
ከምርጫው በማግለል ምርጫውን ህገወጥ አደረግን ማለት አይችሉም። ህዝብ እስከተሳተፈ ምርጫው
ህጋዊ ነው። አብላጫ ድምጽ ያገኘውም ፓርቲ ህጋዊ አሸናፊ ፓርቲ ነው። የተባበሩት መንግስታትም ሆነ
የምዕራቡ ዓለም መስፈርት የሚለው ይኽንኑ ነው። (ስድስቱ የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ሰላማዊ ትግል
101 በሚል ስያሜ በቅርብ ገበያ ላይ በዋለችው መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው ቀርቧል።)
(2) በምርጫ በስልጣን ላይ ያለን መንግስት ህጋዊነት ማሳጣት የሚቻለው የመንግስት ስልጣን ባለቤት
የሆነው ህዝብ እራሱን ከምርጫ ሲያገል ብቻ ነው። አንድ ህዝብ በምርጫ አልሳተፍም ካለ ምርጫ
የለም። አሸናፊ ፓርቲ የሚባልም ነገር የለም። ስለዚህ ህዝብ ከሚሳተፍበት ምርጫ እራሳቸውን ብቻ
በማግለል (ቦይኮት በማድረግ) ምርጫውን ወይንም አሸነፈ የሚባለውን ፓርቲ ህጋዊነት እናሳጣዋለን
ብለው የሚያስቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ የአስተሳሰብ ዝንፈት ወይንም ጨቅላነት አለባቸው። ህዝብን
ሊተኩ ወይንም እራሳቸውን ከህዝብ በላይ አድርገዋል ማለት ነው። አምባገነንነትም በልጅነቱ ይኽንኑ
ነው የሚመስለው።
(3) ዴሞክራሲ በሰረጸባቸው እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ አይነት አገሮች ውስጥ ምርጫ ህዝብ የመንግስት
ስልጣን ባለቤት መሆኑ ማረጋገጫ መንገድ ነው። በእነዚህ አገሮች ምርጫ ቦርዱም ሆነ የህዝብ ታዛቢዎች
(የምርጫ አስፈጻሚዎች) ገለለተኛ በመሆናቸው የመራጩ ህዝብ ድምጽ ይሰረቃል የሚል ስጋት የለም።
የምርጫ ፓርቲዎች ድምጽ ለማስከበር በሚል የሚያደርጉት ስትራተጂያዊ ዝግጅት አይኖርም።
(4) ዴሞክራሲ በሰረጸባቸው እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ አይነት አገሮች ውስጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ
ፓርቲዎች ህዝባቸው እንዲመርጣቸው ስለሚጠይቁ ፓርቲዎቹ የመንግስት ስልጣን ባለቤት
አለመሆናቸውንም ማረጋገጫ ነው ምርጫ። ህዝብ የመንግስት ስልጣን ባለቤት በመሆኑ ከተፎካካሪ
ፓርቲዎች ውስጥ የፈለገውን ይቀጥራል (ይመርጣል)። ያልፈለገውን አይመርጥም (አይቀጥርም)።
በእነዚህ አገሮች ከሞላ ጎደል ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይደረጋል። ስለዚህ በእነዚህ አገሮች ምርጫ
የዴሞክራሲ መገለጫ ነው።
(5) ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ ምርጫ የህዝብን የመንግስት ስልጣን
ባለቤትነት ማምጫ መንገድ ነው። በእነዚህ አገሮች ፥ (ሀ) ሶስቱ የመንግስት ዘርፎች የተነጣጠሉ
ባለመሆናቸው፣ (ለ) የኢትዮጵያ ህገ መንግስት እንባ ጠባቂ ብሎ ያሚጠራው ተቋም ነፃ ባለመሆኑ፣ (ሐ)
በዘልማድ አራተኛው የመንግስት ዘርፍ ተብሎ የሚጠራው ነፃ ፕሬስ እንደልቡ በነጻነት መንቀሳቀስ
ባለመቻሉ፣ (መ) በመንግስት እና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባው ቀጭን ቀይ መስመር ባለመኖሩ፣
(ረ) ምርጫ ቦርዱም ሆነ የህዝብ ታዛቢዎች (የምርጫ አስፈጻሚዎች) ገለለተኛ ባለመሆናቸው ነፃ እና
ፍትሃዊ ምርጫ የደረጋል ብሎ ማሰብ ላም ባልዋለበት ኩበት መልቀም ይቻላል ብሎ እንደማመን ነው።
በእነዚ አገሮች ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ይደረግ የሚለው ጥያቄ የሚቀርበው እንደ መታገያ አሳብ መሆኑ
ታውቆ የምርጫ ፓርቲዎች ከምርጫ ሳይወጡ ህዝባቸውን የመንግስት ስልጣን ባለቤት ለማድረግ
ማለትም ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የጀመሩትን ጉዙ መቀጠል አለባቸው። ስለዚህ ነው በእነዚህ አገሮች
በሚደረግ ምርጫ የምርጫ ስትራተጂ ሲቀየት የህዝብ ድምጽ እንዳይሰረቅ ለማድረግ የሚያስችል
ዝግጅት በስትራተጂ ውስጥ የሚካተተው።
(6) ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ
ምርጫ ካልተደረገ በሚል ምክንያት ከምርጫ መውጣት ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ) ጭንቀት መቀነስ
ብቻ ሳይሆን ደስታን መለገስ ነው። ባቄላ አለቀ ቢባል ፈስ ቀለለ እንደሚባለው ነው የሚሆንለት
ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ)። ምክንያቱም የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ
በምርጫ እስከተሳተፈ ድረስ ምርጫው ህጋዊ ነው። ያሸነፈውም ፓርቲ ወዲያው አለም አቀፍ እውቅናን
ያገኛል። የገንዘብ እና የቁሳቁስ እርዳታም ይቀጥላል። ይኼን ሃቅ ቀደም ብለው በኢትዮጵያ የተደረጉት
አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች አስተምረውናል።
(7) ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ በመሳተፍ የህዝብን
ድምጽ ማግኘት ግን ለኢህአዴግ (ገዢው ፓርቲ) መከራ እና ጭንቀትን ይፈጥራል። ይኽን ሃቅ በምርጫ
97 ያስተዋልነው ነው። ሽንፈትን አልቀበልም ካለ ድምጽ ይከበር የሚል እንቅስቃሴ ሊፈጠር ይችላል።
ይኽንንም ሃቅ በምርጫ 97 አይተናል። አንዴ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከዚያ ወዴት እንደሚሄድ
መገመት አዳጋች ነው። ስለዚህ የምርጫ ፓርቲዎች ለዚህ አይነት አጋጣሚም ቀደም ብለው መዘጋጀት
ይበጃቸዋል። አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጠብቂ በሚለው መመራት ጠቃሚ ነው።
(8) ዴሞክራሲ ባልሰረጸባቸው አገሮች ህዝብ ድምጽ የመሰረቅ እድሉ ከፍተኛ ነው። በሰላማዊ ትግል የህዝብ
ነፃ አውጭ እራሱ ህዝቡ መሆኑ ታውቆ የምርጫ ፓርቲዎች እምነታቸው በውጭ አገር ድጋፍ ወይንም
በምርጫ ቦርድ ሳይሆን በህዝብ ላይ መሆን አለበት። ስለዚህ የምርጫ ፓርቲዎች ህዝብ ድምጹን
እንዳይሰረቅ ማድረግ እንዲችል ማሰልጠን እና ማደራጀት አለባቸው። የምርጫ ፓርቲዎች ማድረግ
ከሚገቧቸው ስራዎች ውስጥ ጥቂቱ የሚከተሉትን ያካትታል፥ (ሀ) በህዝብ ታዛቢዎች ላይ ገለልተኛ
እንዲሆኑ ጫና በማሳደረ፣ (ለ) ለምርጫ እድሜው የደረሰ በሙሉ ለምርጫ እንዲመዘገብ እና የምርጫ
ካርድ እንዲወስድ በማድረግ፣ (ሐ) ህዝቡ የምርጫ ካርዱን የሚቀጥሉት አምስት አመቶች በአገሩ
አቅጣጫ ላይ ውስኔ መስጫው መብቱ መተግበሪያ አድርጎ እንዲያምን በማድረግ፣ (መ) በምርጫ እለት
የምርጫ ካርድ የወሰደ መራጭ በሙሉ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ በማሳመን፣ (ሠ) በምርጫው ዕለት
በድስፕሊን የታነጹ እና በምርጫ ህግ የሰለጠኑ የእምነት ጽናት ያላቸው የእጩ ታዛቢዎች በየምርጫ
ጣቢያው በማሰማራት ታህሳስ 12/2007 ተመረጡ የተባሉት የህዝብ ታዛቢዎች በእድሜ የገፋውን
መራጭ ህዝብ ሳያደናግሩ የምርጫ ካርዶችን እና የምርጫ ኮሮጆዎችን በገለልተኛነት እንዲያስተናግዱ
በመከታተል፣ (ረ) እጩዎች ህዝቡ እንዲመርጣቸው የሚያደርጉ መልዕክቶች፣ የትምህርት ደረጃ፣ ማራኪ
ባህሪ፣ ተወዳጅነትም እንዲኖራቸው በማድረ (ማሰልጠን ይቻላል)፣ (ሰ) ገዢው ፓርቲ ከሽንፈት ማምለጫ
መከራከሪያ እንዳይኖረው እና ሽንፈትን ሳያንገራግር እንዲቀበል ለማድረግ ይቻል ዘንድ በሚሸነፍባቸው የምርጫ
ጣቢያዎች እና የምርጫ ክልል ወረዳዎች ሽንፈቱ በከፍተኛ ድምጽ (landslide) እንዲሆን ማድረግ (ሸ) የምርጫ
ጣቢያዎች ሲዘጉ ድምጽ ተቆጥሮ አሸናፊ እስኪታወቅ መራጩ ህዝብ ከየምርጫ ጣቢያዎች ርቆ
እንዳይሄድ ማድረግ። የህዝብ ድምጽ ከተሰረቀ መራጩ ህዝብ ድምጼን ካላከበርክ እኔም የአንተን ገዢነት
አላከብርም የሚል እንቅስቃሴ ሊጀምር ይችላል። ስለዚህ በእነዚህ አገሮች የሚደረግ ምርጫ በአግባቡ
ከተያዘ እና ከተመራ የህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤትነት ማምጫ መንገድ ነው። ዴሞክራሲን
ማምጫ ነው።
(9) ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ የሚደረግ ጠብመንጃ-መር ትግል
(ለምሳሌ፥ ትጥቅ ትግል፣ የከተማ ግድያ፣ ሽብር፣ በፕላን ያልተመራ ሰላማዊ አመጽ፣ ወ.ዘ.ተ. ) አምባገነን
ማምጫ ነው።
(10)ዴሞክራስ ባልሰረጸባቸው እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገሮች ውስጥ በሚደረግ ምርጫ የምርጫ ፓርቲዎች
በተካሄደው ምርጫ የተገኙ ፖለቲካዊ እና ድርጅታዊ ድሎችን መልቀም የሚያስችሉ ዝግጅቶች ቀደም
ብለው ማድረግ አለባቸው። ይኽን ለማድረግ በቅድመ-ምርጫ ዝግጅት፣ በምርጫ እለት እና ከምርጫ
ማግስት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን (Scenarios) ቀደም ብለው መተንተን እና ቀዳዳዎችን መድፈን
የሚያስችሉዋቸው ዝግጅቶች ማድረግ አለባቸው። በምርጫ 2007 የተገኙ ድሎች እንደ ምርጫ 1997
መባከን የለባቸውም። ገዢውን ፓርቲ ሊያስበረግጉ እና ሊያስቆጡ ከሚችሉ ድንፋታዎች፣ ዛቻዎች፣
ፉከራዎች፣ ትንኮሳዎች፣ መፈጸም የለባቸውም ተቃዋሚ የምርጫ ፓርቲዎች። ገዢው ፓርቲ ሽንፈት
በደረሱበት አካባቢዎች ሽንፈትን የጀግኖች ሽንፈት አድርጎ መቀበል የተሻለ አማራጭ አድርጎ እንዲዎስድ
ማበረታታት ያስፈልጋል።
ግርማ ሞገስ
No comments:
Post a Comment